ባህላዊ ፍርድ ቤት ፍትህን በቅርበት ለማግኘት እና አለመግባባቶች በእርቅና በስምምነት እንዲፈቱ አስችሏል

አምቦ፤ ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፡-በአካባቢያቸው የተቋቋመው ባህላዊ ፍርድ ቤት ፍትህ በቅርበት እንዲያገኙ ከማስቻሉም ባለፈ አለመግባባቶች በእርቅና በስምምነት እንዲፈቱ እያደረገ መሆኑን የምእራብ ሸዋ ዞን ዳኖ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።

የኦሮሚያ ክልል ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን በየአካባቢው በማቋቋም ህዝቡ በነባር ባህላዊ እሴቶቹ ጭምር ታግዞ ፍትህን እንዲያገኝ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።

ባህላዊ ፍርድ ቤቶቹ ህብረተሰቡ ከአካባቢው ሳይርቅ ፍትህ እንዲያገኝ ከማስቻሉም በተጨማሪ መደበኛ ፍርድ ቤቶች ላይ የነበረውን ጫና መቀነስ ማስቻላቸውን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይገልጻል።

ኢዜአ ያነጋራቸው የምእራብ ሸዋ ዞን ዳና ወረዳ ነዋሪዎችም በባህላዊ ፍርድ ቤቱ አማካኝነት ፍትህን በቅርበት እያገኙ አለመግባበቶችን በእርቅና በስምምነት እየፈቱ መሆኑን ተናግረዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ኢብራሂም ጅማቶ እንዳሉት፣ ባህላዊ ፍርድ ቤቱ ከመቋቋሙ በፊት ፍትህን ለማግኘት የወረዳው ዋና ከተማ ድረስ በመመላለስ ጊዜና ገንዘባቸውን ያባክኑ ነበር።

ካለፈው ዓመት ጀምሮ ግን ባህላዊ ፍርድ ቤቱ አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ፍትህን በቅርበት ማግኘት በመቻላቸው ጊዜያቸውን በልማት ስራዎች ላይ እያዋሉ መሆኑን ተናግረዋል።

ባህላዊ ፍርድ ቤቱ በተለይም ፍትህን በቅርበት ተደራሽ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ጉዳያቸው በእርቅና በስምምነት እንዲያልቅ ጭምር እድል እንደፈጠረላቸውም ገልጸዋል።

ባህላዊ ፍርድ ቤቱ የፍትህ ጉዳያቸው ፈጥኖ መቋጫ እንዲያገኝ ከማስቻሉም በላይ ችግሮች በስምምነት ስለሚፈቱ ቂምና ቁርሾ እንዳይኖር ማድረጉን የገለጹት ደግሞ አቶ ታዬ በቀለ ናቸው።

ይህም በህብረተሰቡ መካከል ሰላም እንዲሰፍንና አብሮነት እንዲጠናከር እያደረገ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።

በወረዳው ዳኖ ሸነኒ ቀበሌ በሚገኝ ባህላዊ ፍርድ ቤት በዳኝነት የሚያገለግሉት አባ ገዳ ኦላኒሳ ነገራ በበኩላቸው በፍርድ ቤቱ የሚሰጠው ባህላዊ ዳኝነት መሰረቱ የገዳ ስርዓት ነው ይላሉ።

የክልሉ መንግስትም ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ስራ እንዲጀምሩ ማድረጉ የሚያስመስግነው ተግባር መሆኑን ገልጸው ፍርድ ቤቱ ለአካባቢው ነዋሪዎች ትክክለኛ ፍትህን ተደራሽ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በተለያየ ምክንያት አለመግባባት ውስጥ የገቡ ግለሰቦች በባህላዊ ፍርድ ቤቱ ላይ እምነት እያሳደሩ፤ ፍትህም እያገኙ መምጣታቸውን ተናግረው በዳኖ ሻናኒ ቀበሌ ባህላዊ ፍርድ ቤት በ2017 በጀት ዓመት 157 አቤቱታዎች ቀርበው 145 የሚሆኑት ውሳኔ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።

የምዕራብ ሸዋ ዞን የከፍተኛ ፍርድ ቤት ተወካይ አቶ ወዬሣ በቃና፣ የባህላዊ  ፍርድ ቤቶቹ መቋቋም በተለይም በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ላይ ያለውን ጫና ያቃልለዋል ብለዋል።

ከዚህ በፊት ሁሉም የህግ ጉዳዮች ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት ይቀርቡ እንደነበረ ገልጸው ባህላዊ ፍርድ ቤቶቹ በዞኑ እስከ ቀበሌ ድረስ በመዋቀራቸው አነስተኛ የሆኑ የህግ ጉዳዮች እዛው እየታዩ ነው ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም