ቀጥታ፡

በመንገድ መሠረተ ልማት ዘርፍ ተግባራዊ እየሆኑ ያሉ ስትራቴጂዎች ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት እያስቻሉ ነው - የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፦ የመንገድ መሠረተ ልማት የግንባታ ጥራት ለማረጋገጥ ተግባራዊ እየሆኑ ያሉ ስትራቴጂዎች ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት እያስቻለ መሆኑን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ የትምጌታ አስራት ገለጹ።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የመንገድ ምርምር ማዕከል ስምንተኛውን የመንገድ ዘርፍ ጉባኤ እያካሄደ ይገኛል።


 

በጉባኤው መክፈቻ ላይ የተገኙት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ የትምጌታ አስራት እንዳሉት፤ መንግስት የኮንስትራክሽን ዘርፉን አቅም ለማሳደግ የሚያስችሉ ንቅናቄዎች በመቅረጽ እየሠራ ነው።

የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ ጥራትና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ስትራቴጂዎች ተግባራዊ መደረጋቸውን ነው የጠቀሱት።

ይህም በመንገድ ግንባታ ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እያስቻለ መሆኑን ተናግረው፤ ይህን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ጥናትና ምርምሮች ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት።

የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታው አቅምንና አፈፃፀምን ማሳደግ ዘላቂ የሆነ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዘርፋ የሚካሔዱ ምርምሮችና ኮንፈረንሶች የተሻሉ ስትራቴጂዎችን ለመቅረፅና ዓለም አቀፋ ተወዳዳሪነት ለማምጣት የሚያግዝ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሀመድ አብዱራህማን በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት መንግስት በተለይ የመንገድ መሠረተ ልማትን ይበልጥ በማጠናከር ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ ነው።

በዛሬው እለት የተካሔደው ያለው የጥናትና ምርም ጉባኤም የጥናት ውጤቶችን ተግባራዊ በማድረግ ዘርፋን አፈፃፀም ለማሳደግ የሚረዳ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም