በዞኖቹ በ2018 የትምህርት ዘመን ለመማር ማስተማር ስራውን የሚረዱ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኖቹ በ2018 የትምህርት ዘመን ለመማር ማስተማር ስራውን የሚረዱ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተከናውነዋል

ጭሮ/ነጌሌ ቦረና፤ ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሐረርጌ ዞን እና ምስራቅ ቦረና ዞን በ2018 የትምህርት ዘመን ለመማር ማስተማር ስራው የሚረዱ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መከናወናቸውን የዞኖቹ ትምህርት ጽህፈት ቤቶቹ ገለጹ።
በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በ2018 የትምህርት ዘመን ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ያሉ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መደረጋቸውን የዞኑ ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ገልጿል።
በዞኑ ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት የትምህርት ባለሙያ አቶ ታከለ ዓለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ በ2018 የትምህርት ዘመን ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች በትምህርት ላይ ይሆናሉ።
በትምህርት ዘመኑ የመማር ማስተማር ስራውን የሚያቀላጥፉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ገልጸው በዚህም በመንግስት በጀት እና በህብረተሰብ ተሳትፎ የተጨማሪ መማሪያ ክፍሎች ግንባታ፣ የመምህራን መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እና የዲጂታል ፓርኮች ግንባታ ሲካሄድ መቆየቱን ገልጸዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን በበጀት ዓመቱ የቅድመ መደበኛ እና አንደኛ ደረጃ የሚማሩ ከ700 ሺህ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ቤቶች ምገባ መርሃ ግብር እንደሚታቀፉ አመልክተዋል፡፡
ከእነዚህ ስራዎች ጎን ለጎን ለቀጣዮቹ 15 ቀናት የሚቆይ የተማሪዎች ምዝገባ ከትናንት ጀምሮ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ በምስራቅ ቦረና ዞን በትምህርት ዘመኑ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
በጽህፈት ቤቱ የእቅድና በጀት ክትትል ቡድን መሪ አቶ በዳዳ ወርቅነህ፣ ከዝግጅቶቹ መካከል የትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻል፣ የመማሪያ ክፍሎችና የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ተካሄደዋል፡፡
በተያያዘም 620 መምህራንና ርዕሳነ መምህራን በትምህርት ሚኒስቴርና በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ወስደው መመለሳቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ስልጠናውን ከወሰዱ መካከል 27 ርዕሳነ መምህራን፣ 113 የ2ኛ ደረጃና 484 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራን ይገኙበታል ብለዋል፡፡
ለበጀት ዓመቱ የመማር ማስተማር ስራም በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች የሚገኙ ከ530 በላይ ትምህርት ቤቶች ዝግጁ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡
ጠሬጴዛ ወንበርና የተለያዩ የትምህርት መርጃ ቁሳቁሶች አቅርቦትና የመምህራን መኖሪያ ቤቶች ግንባታም የዝግጁቱ አካል እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡
በዞኑ በጎ ፈቃደኞች እስካሁን የሁለት ትምህርት ቤቶች ደረጃ መሻሻሉንና የ46 የመምህራን መኖሪያ ቤቶች በግንባታ ላይ እንዳሉም አስታውቀዋል፡፡