ቀጥታ፡

ይፋ የተደረገውን የደመወዝ ጭማሪ ተከትሎ በክልሉ በሸቀጦች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፦ መንግስት ይፋ ያደረገውን የደመወዝ ጭማሪ ተከትሎ በምርቶች እና ሸቀጦች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግ ቅንጅታዊ አሰራር ተዘርግቶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ንግድ ቢሮ አስታወቀ።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መንግሥት ከመስከረም ወር ጀምሮ ተግባራዊ የሚያደርገውን የደመወዝ ጭማሪ ተከትሎ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ ጥብቅ እርምጃ ይወሰዳል ማለቱ ይታወሳል።

ይህንኑ መነሻ በማድረግ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኦሮሚያ ክልል ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ገሾ እንደተናገሩት ከደመወዝ ጭማሪ ጋር ተያይዞ በምርቶች እና በፍጆታ እቃዎች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግ የተቀናጀ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።

ለዚህም በየአካባቢው በቂ ምርት ከማቅረብ ጎን ለጎን ከክልሉ እስከ ቀበሌ ድረስ ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ከመደበኛ ገበያዎች በተጨማሪ ስራ በጀመሩ 594 የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች አማካኝነት ምርት እየቀረበ ይገኛል ብለዋል።

በተለይም በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር እና በከተማ ግብርና የሚመረቱ ምርቶች በገበያዎቹ በቀጥታ እንዲቀርቡ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም የኢንዱስትሪ ምርቶችም በቀጥታ በፋብሪካ ዋጋ እየቀረበ መሆኑን አመልክተዋል።

በክልሉ ከተሞች “ከኢትዮ ይግዙ’’ በሚል ዐውደ ርዕይና ባዛር ተዘጋጅቶ ሰፊ የግብርና ምርቶችና የኢንዱስትሪ ውጤቶች ቀርበው ግብይቱ ከመደበኛ ዋጋ በታች በሆነ ዋጋ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

በተለይ በትራንስፖርት ዘርፍ፣ በግብርና ምርቶች፣ በኢንዱስትሪ ውጤቶችና ከግንባታ እቃዎች ጋር ተያይዞ ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ዋጋን የሚጨምሩ ተቋማት ላይ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን አንስተዋል።

በተመሳሳይም ምርቶችን በሚደብቁ ነጋዴዎች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸው፤ የምርት ዝውውሩ እንዲሳለጥ ከጸጥታ አካላት በቅርበት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በክልሉ ህገወጥ ንግድን በቀጣይነት ለመከላከል የዘርፉ ባለሙያዎችን ያካተተ ግብረ ኃይል እስከ ታችኛው የአስተዳደር መዋቅር ድረስ መደራጀቱንም ነው የገለጹት።

ባለፈው በጀት ዓመት ከ186 ሺህ በላይ በሚሆኑ ህገወጥ ነጋዴዎች ላይ የተለያየ እርምጃ ተወስዶባቸው ወደ ህጋዊ መስመር እንዲገቡ መደረጉንም አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም