ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮዽያ ህዳሴ ግድብ የጋራ ትርክት ግንባታ መሰረትና የሀገራዊ ስኬት ማሳያ ነው

ሐረማያ፤ ነሐሴ 22/2017 (ኢዜአ) ፡-ታላቁ የኢትዮዽያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያዊያን አዲስ ታሪክ የፃፉበት፤ የጋራ ትርክት ግንባታ መሰረትና የሀገራዊ ስኬት ማሳያ መሆኑን በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ገለጹ።

የህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ በሁሉም አቅጣጫ ኢትዮጵያዊያን ህብረ ብሄራዊ አንድነታቸውን በማሳየት በገንዘብ፣ በጉልበትና ለየትኛውም ጫና ባለመበገር ከፊት በመቆም የገነቡት ፕሮጀክት መሆኑ ይታወቃል።

በሀገር ውስጥና በውጭ ግንባታውን ለማደናቀፍ የጣሩ አካላት ቢኖሩም በአልበገርም ባይነት ለስኬት በማብቃት አዲስ ታሪክ መስራት የተቻለበት አጋጣሚ ተፈጥሯል።

በዚሁ ሁሉ ሂደት የመንግስት የዲፕሎማሲ ጥረት፣ የህዝቡ ትብብርና አንድነት በተግባር የታየበት መሆኑም ይታወቃል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የጋራ ትርክት ግንባታ መሰረትና የሀገራዊ ስኬት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በውሃ ሃብት እና አካባቢ ምህንድስና ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ኤልያስ ጀማል (ዶ/ር) የግድቡ መገንባት ከኢትዮጵያም ባለፈ የቃጣናውን አገራት በኃይል ልማት ማስተሳሰር የሚያስችል ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑን አንስተዋል።

ለኢንዱስትሪዎች መስፋፋት፣ ለቱሪዝም ሃብት መጎልበት፣ ለተፈጥሮ መስህብ ጥበቃና ለዓሳ ሃብት ልማት ጭምር እሴት መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያን በራስ አቅም ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እውን ማድረግ እንደሚችሉ በተግባር የታየበት፣ ሀገራዊ የልማት ስኬት የጋራ መገለጫና የጋራ ትርክት መሰረት ያኖረ ቋሚ ቅርስ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን እና በኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል  መምህር  አራርሳ አበራ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከሃይል ምንጭነትም ባለፈ የሀገር እድገት መሰረትና የብዙ ሃብቶች ምንጭ የሚሆን ነው ብለዋል።

በአካባቢው የዓሳ ሃብት ልማት ምርታማነትን ለማሳደግና የቱሪስት መስህብ ስፍራ በመሆን ለትውልድ የሚተላለፍ የሀገር ሃብት መሆኑንም አንስተዋል።

ግድቡ የህብረ ብሄራዊ አንድነት ምልክት፣ የመቻልና የመፈፀም አቅም የታየበት መሆኑንም ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም