በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በተሰሩ ስራዎች አበረታች ውጤቶች ተገኝተዋል

ድሬደዋ፤ ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፦ ለሀገር እድገት የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ጥቅም ላይ በማዋል አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ተናገሩ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት እንዲሁም የክልሎች የዘርፉ ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም እና የተያዘው በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ ላይ በድሬደዋ እየተወያዩ ነው።


 

በውይይቱ ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ የአገርን ከፍታና ዕድገት ለማረጋገጥ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በስፋትና በጥራት ስራ ላይ ማዋል ትኩረት ተሰጥቷል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችና የፈጠራ ስራዎችን ወደ ተግባር በማሸጋገር በተቋማት በቴክኖሎጂ የታገዙ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎቶች በመስጠት አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል።

የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶች በመዘርጋትና ከክልሎች ጋር በመቀናጀት ረገድ በተከናወኑ ተግባራትም አብነታዊ ስራዎች መሰራታቸውን በማስታወስ።

ከነዚህ በተጨማሪም የ'ስታርት አፕ' አዋጅ ፀድቆ ወደ ተግባር መሸጋገሩ የቴክኖሎጂ ፈጠራና ትውልዱ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት የድርሻውን እንዲወጣ መነቃቃት መፍጠሩን ተናግረዋል።

በሰው ኃይል ልማትና ክህሎትም የአምስት ሚሊየን ኢትዮ- ኮዲንግ ስልጠናን ዜጎች በመውሰድ የዲጂታል ዕውቀታቸውን እንዲያሳድጉ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የሚፈለገውን ተወዳዳሪና ውጤታማ ዜጋ የማፍራቱን ሂደት ያጠናክረዋል ብለዋል።


 

በድሬዳዋ የተጀመረው ውይይት እንደ አገርም ሆነ እንደ ድሬደዋ የተገኙ ውጤቶችን ለማጠናከር እና የተሻለ ለውጥ ለማምጣት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ያሉት ደግሞ በውይይቱ የተሳተፉት የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ ናቸው።

ምክትል ከንቲባው አክለው እንዳሉት በድሬዳዋ አስተዳደር ተቋማት የዲጂታል ቴክኖሎጂ እና አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶችን በመጠቀም ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎቶች ለህዝብ ተደራሽ እየተደረገ ነው።

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ውይይት ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች፣ እንዲሁም የክልሎች የዘርፉ አመራሮች ተሳታፊ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም