የህብረተሰቡን የፍትህ ጥያቄዎች ለመመለስ በተሰሩ ስራዎች አበረታች ውጤቶች ተገኝተዋል

ድሬደዋ፣ ነሐሴ 22/2017 (ኢዜአ) የህብተረሰቡን የፍትህ ጥያቄዎች በተጨባጭ ለመፍታት እና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ስራዎች አበረታች ለውጦች መገኘታቸውን የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነ ብርሃን (ዶ/ር) ተናገሩ።

ስምንተኛው የፍትህ ሚኒስቴርና የክልሎች የፍትህ ቢሮዎች የጋራ ጉባዔ "የህግ የበላይነትና ሰብዓዊ ክብርን ያረጋገጠ ተአማኒ የፍትህ ስርዓት እንገነባለን" በሚል መሪ ሐሳብ ዛሬ በድሬደዋ ተጀምሯል።


 

ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚሁ ጉባዔ ላይ የዘርፉ የተጠቃለለ ሀገራዊ  የ2017 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም እና የተያዘው በጀት ዓመት መሪ እቅድ ይገመገማል።

በጉባዔው ላይ የተሳተፉት የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነ ብርሃን (ዶ/ር) በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን በተሳካ መንገድ በመተግበር የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የተቀናጀ ርብርብ ተደርጓል።

በተለይ በሶስት ዓመቱ የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተቀመጡ ዕቅዶችን መሠረት በማድረግ የተሰሩ ስራዎች የህብረተሰቡን የፍትህ ጥያቄዎች ለመመለስ ያስቻሉ ናቸው ብለዋል።

የህግ ማዕቀፍ፣ የተቋምና የአሰራር ስርዓቶችን በመቅረፅ እንዲሁም የለሙ የቴክኖሎጂ ሲስተሞች ላይ ልምዶችን በማካፈል የተሻለ ስራ መሰራቱንም አክለዋል።

በተጨማሪም ተአማኒ የፍትሕ ስርዓትን በመገንባትና ሰብዓዊ ክብርን በማረጋገጥ አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን አንስተዋል።

እነዚህን የተገኙ ውጤቶች ተቀናጅቶ ለማስቀጠል የተጀመሩት የሕግ የበላይነትና ተአማኒ የፍትህ ስርዓትን የመገንባት ጉዞን አጠናክሮ ለማስቀጠል ዛሬ የተጀመረው ጉባዔ ጥሩ መዳላድል ይፈጥራል ብለዋል።


 

በጉባዔው የታደሙት የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአስተዳደሩ የዜጎችን የፍትህ ጥማት ለማርካት በቴክኖሎጂ የታገዙ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።

በድሬዳዋ የተጀመረው ሀገራዊ ጉባዔ እነዚህን ውጤቶች በተሻለ ፍጥነትና ጥራት ወደ ከፍታ ለማድረስ ብዙ ልምድና ተሞክሮ የሚቀሰምበት መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ሀገር በዘርፉ የተገኙ ውጤቶችን በተቀናጀ እና በተናበበ መንገድ ለማሸጋገር መደላድል የሚፈጥር መሆኑንም እንዲሁ።

ዛሬ በተጀመረው ጉባዔ ላይ የፍትሕ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች እና የየክልሎች የፍትሕ ዘርፍ መሪዎች እና የፀጥታ አካላት ከፍተኛ ኃላፊዎች  ተሳታፊ ናቸው ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም