ሴቶችን ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
ሴቶችን ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፦ በተለያዩ የስራ መስኮች ሴቶችን ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ አስታወቀ።
የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ ምክር ቤት የ2017 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም እና የ2018 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ውይይት እያካሄደ ነው፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ ዋና ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ወይዘሮ መዓዛ ካሚቶ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተለያዩ መስኮች የሴቶችን ተጠቃሚነት ያጎሉ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
ከስራ ዕድል ፈጠራ እና በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ዙሪያ የሴቶችን ግንዛቤ በማሳደግ በመርሃ ግብሩ እንዲሳተፉ የሚያስችሉ አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡
ለአብነትም በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር አምስት ሚሊዮን ሴቶችን ለማሳተፍ ግብ መያዙን አስታውሰው፤ አምስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሴቶች በመርሃ ግብሩ እንዲሳተፉ መደረጉን ገልፀዋል፡፡
በአቅመ ደካማ ቤቶች ግንባታ እና እድሳት፣ በማዕድ ማጋራት፣ በደም ልገሳ እንዲሁም በጎ ፈቃድ ስራዎች የጎላ ተሳትፎ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል ፡፡
እንደ ወይዘሮ መዓዛ ገለጻ፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ክንፉ ለሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል ፡፡
በዘላቂ ሰላም ግንባታና በአገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ሴቶችን በማሳተፍ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከአባላቱ በንቅናቄ ከ185 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡንም ለአብነት አንስተዋል ፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የክንፉ ዋና ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ መስከረም አበበ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በቀጣይ የሴቶችን አቅም በማሳደግ የፖለቲካ ተሳትፏቸውን የማሳደግ ስራ በትኩረት ይከናወናል፡፡
ቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያ በሆነ መንገድ እንዲከናወን በሚደረገው ጥረት የሴቶች ሚና ትልቅ ነው ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቷ፤ በቀጣዩ ምርጫ ሴቶች የጎላ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ይሰራል ብለዋል፡፡