ኢትዮጵያ በአፍሪካ አየር ንብረትና በአፍሪካ-ካሪቢያን ጉባኤዎች አህጉራዊ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ መሪ ሚናዋን ትወጣለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ አየር ንብረትና በአፍሪካ-ካሪቢያን ጉባኤዎች አህጉራዊ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ መሪ ሚናዋን ትወጣለች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አየር ንብረትና በአፍሪካ-ካሪቢያን ጉባኤዎች ብሔራዊና አህጉራዊ ጥቅሞችን የሚያስጠበቁ አጀንዳዎችን በማቅረብ መሪ ሚናዋን እንደምትወጣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ገለጹ።
አምባሳደር ነብያት በወቅታዊ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች በሰጡት መግለጫ፤ኢትዮጵያ የአፍሪካ ካሪቢያን ማህበረሰብ እና ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤዎች በስኬት ለማስተናገድ ዝግጅት ማድረጓን ገልጸዋል።
ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ አፍሪካ በብራዚል በሚካሄደው 30ኛው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ የራሷን ድምፅ ይዛ የምትቀርብበትን ዕድል እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ በሚከናወነው ጉባኤ ከ25 ሺህ በላይ ታዳሚዎች እንደሚሳተፉ ገልጸው፣ አፍሪካውያን የአየር ንብረት ለውጥን ተፅዕኖን ለመቋቋም የጋራ የሆነ አፍሪካዊ ስልት የሚቀይሱበት መድረክ እንደሚሆንም ተናግረዋል።
ከዚህም ባሻገር የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም ዓለም አቀፍ ፋይናንስ ለማፈላለግ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በጉባኤው ሀገራዊና አህጉራዊ አጀንዳን በማቅረብ መሪ ተዋናይ እንደምትሆን ጠቅሰው፥ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን የመከላከል ውጤታማ ተሞክሮዋን እንደምታካፍልም አንስተዋል።
በተጨማሪም የአፍሪካ ካሪቢያን ማህበረሰብ ጉባኤ "ለአፍሪካውያንና ዘርዓ አፍሪካውያን የማካካሻ ፍትህን ለመሻት አህጉር ተሻጋሪ አጋርነት" በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄድ ሲሆን የጋራ ድምፅ ማሰማት እንዲችሉ መሰረት እንደሚሆን ገልጸዋል።
ጉባኤው የአፍሪካና ካሪቢያን ሀገራት በደቡብ ደቡብ የትብብር መንፈስ ግንኙነታቸውን ለማጎልበት፣ አፍሪካ ከካረቢያን ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ጠንካራ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ እና ትብብር ለማሳደግ ያስችላታል ብለዋል።
ጉባኤው በዓለም የፋይናንስ ስርዓት፣ በቱሪዝም፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ እንደሚመክር ገልጸው፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የካሪቢያን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ባሉ የኢንቨስትመንት ዕድሎች እንዲሰማሩ ይደረጋል ነው ያሉት።
አምባሳደር ነብያት በመግለጫቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን ማንሰራራት የሚያበስር ትልቅ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ለቅኝ ግዛት እሳቤዎች ቦታ የላትም ያሉት አምባሳደር ነብያት፣ በጋራ ተጠቃሚነትና ልማት ላይ የተመሰረተ ፅኑ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑክ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተላከ መልዕክትን ለደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ማድረሱን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም በሁለቱ ሀገራት ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ትብብር መሰረት በኃይል፣ አቪየሽን፣ በመንገድ ስራና ሌሎች ዘርፎች በጋራ መስራት የሚያስችል ፍሬያማ ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።
ይህም ኢትዮጵያ በቀጣናው ልማትና ትብብር ያላትን የተግባር እርምጃና ጽኑ አቋም የሚያሳይ ነው ብለዋል።