መንግሥት በተሀድሶ ስልጠና የሚያልፉ የቀድሞ ታጣቂዎች የልማትና የሰላም ግንባታ አካል እንዲሆኑ በትኩረት እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት በተሀድሶ ስልጠና የሚያልፉ የቀድሞ ታጣቂዎች የልማትና የሰላም ግንባታ አካል እንዲሆኑ በትኩረት እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፦ መንግሥት በተሀድሶ ስልጠና የሚያልፉ የቀድሞ ታጣቂዎች የልማትና የሰላም ግንባታ አካል እንዲሆኑ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለጹ።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን በበኩላቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች በተሀድሶ ስልጠና በማሳለፍ ወደ ማህበረሰባቸው እንዲቀላቀሉ መደረጉን አስታውቀዋል።
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የመንግስትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎችን በደብረ ብርሐን ጊዜያዊ የዲሞብላይዜሽን ማዕከል በተሀድሶ ስልጠና መልሶ የማቋቋም ስልጠና መሰጠት ተጀምሯል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥ መንግስት ምንጊዜም ሰላምን ለማጽናት ዝግጁ ነው።
ለዚህም የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ማህብረሰቡ እንዲቀላቀሉ እንዲሁም የልማትና የሰላም ኃይል እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
በአማራ ክልልም በተለያዩ የተሀድሶ ማዕከላት ከፍተኛ በጀት በመመደብ የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሀድሶ ስልጠና በማሳለፍ መደበኛ ህይወታቸውን እንዲመሩ መንግሥት ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።
በተሀድሶ ስልጠና የሚያልፉ የቀድሞ ታጣቂዎችም በቀጣይ ህይወታቸው ህዝብና ሀገራቸውን መካስ እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።
በተሳሳተ መንገድ በጫካ የሚገኙ የታጠቁ አካላት የመንግስትን ጽኑ የሰላም ፍላጎት በመቀበል ወደሰላም እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን፥ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ72 ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች በተሀድሶ ስልጠና አልፈው ወደ ማህበረሰባቸው እንዲቀላቀሉ መደረጉን ገልጸዋል።
የተሀድሶ ስልጠናው ለልማትና ለሰላም ግንባታ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በአማራ ክልል በ2ኛው ዙር በደብረ ብርሐን፣ በኮምቦልቻና ጎንደር ጊዜያዊ የተሀድሶ ማዕከላት ከ6 ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ተሃድሶ ስልጠና መግባታቸውን ተናግረዋል።
የመንግስትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች የሰላም አምባሳደሮች እንደሆኑም አንስተዋል።
በተሀድሶ ስልጠና ማስጀመሪያ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የጸጥታ ተቋማት አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።