በደቡብ ወሎ ዞን በክረምት ወራት ከ586 ሚሊዮን ብር በላይ የሚተመን የበጎ ፈቃድ ተግባርን ማከናወን ተችሏል

ደሴ ፤ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፡- በደቡብ ወሎ ዞን በክረምት ወራት ከ586 ሚሊዮን ብር በላይ የሚተመን የበጎ ፈቃድ ተግባርን ማከናወን መቻሉን የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የወጣቶች ማካተት፣ ንቅናቄና ተሳትፎ ቡድን መሪ አቶ ምስጋናው ደምሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በክረምቱ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ወጣቱን በማሳተፍ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት ተሰርቷል።

በዞኑ ከ969 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ በተካሄደው እንቅስቃሴ እስካሁን ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

የተከናወኑ ተግባራትም 317 የአቅመ ደካሞች አዲስ ቤት ግንባታ፣ ከ1 ሺህ 600 በላይ ቤቶች ጥገና፣ የ127 ሚሊዮን ችግኝ ተከላና 1 ሺህ 632 ዩኒት ደም ልገሳ እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከ6 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አቅመ ደካማ ወገኖች ነጻ ሕክምና፣ ከ8 ሺህ 700 በላይ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት መሰጠቱን ጠቁመው የአቅመ ደካሞችን መሬት በዘር የመሸፈንና የመንከባከብ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

የተከናወነው ተግባር በገንዘብ ሲተመን ከ586 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን  ጠቁመው የተገኘው አበረታች ውጤት እስከ መስከረም ወር 2018 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በደሴ ዙሪያ ወረዳ የ038 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ እቴነሽ አባቡ በበኩላቸው መኖሪያ ቤታቸው በአገልግሎት ብዛት አርጅቶ በመፍረሱ ሲቸገሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቤታቸው በአዲስ ተሰርቶላቸው ከችግራቸው በመላቀቃቸው መደሰታቸውን ጠቁመው ለሰሩትና ላስተባበሩት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

"አቅመ ደካማ በመሆኔ ቤቴ አርጅቶና ፈርሶ በዝናብ፣ በአቧራ፣ በንፋስና በብርድ ስሰቃይ ኑሬያለሁ" ያሉት ደግሞ በተሁለደሬ ወረዳ የ03 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አሚናት በዛብህ ናቸው።

ሰሞኑን በበጎ ፈቃደኞች ታድሶልኝ ከነበረብኝ ችግር ተላቅቄ እፎይታ አግኝቻለሁ ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም