ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና ዳንጎቴ ግሩፕ ለማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክት ግንባታ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና ዳንጎቴ ግሩፕ በ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ለሚገነባው የማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክት ግንባታ ዛሬ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ወደ ምግብ ዋስትና እና የግብርና ሽግግር በምናደርገው ጉዞ አንድ ሌላ እጥፋት ላይ በመድረሳችን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ እንኳን ደስ አለን ሲሉ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና በዳንጎቴ ግሩፕ መካከል የማዳበሪያ ማምረቻ ኮምፕሌክስ የድርሻ ስምምነት ዛሬ መፈረሙን ጠቁመዋል።


 

2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት እንደሚፈስበት ሜጋ ፕሮጀክት በአመት እስከ ሶስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ እንደሚያመርትና ይኽም ኢትዮጵያን ከአለም ግንባር ቀደም አምራቾች አንዷ እንደሚያደርጋት አመልክተዋል።

ፕሮጀክቱ በሀገር ውስጥ የሥራ እድል የሚፈጥርና ለዘመናት ለተፈተኑት ገበሬዎቻችን አስተማማኝ የማዳበሪያ አቅርቦት ያረጋግጣል ነው ያሉት።

ለምግብ ሉዓላዊነት መንገዳችንም ወሳኝ ርምጃ መውሰዳችንን ያመላክታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመላው አኅጉሩ ኢትዮጵያ ያላትን ተወዳዳሪነት በማጠናከር ሕዝባችንን እና ነጋችንን የሚጠቅሙ ስትራቴጂክ ኢንቨስትመንቶችን የመከወን ጽኑ አቋማችንን ያሳያል ሲሉም ገልጸዋል።

የዛሬውን የፊርማ ስምምነት ተከትሎ ፋብሪካው በሚቆምበት ስፍራ ፕሮጀክቱን በይፋ እንደሚጀመር ጠቁመዋል።

ይኽን ታሪካዊ ጉዞ ጀምረናል። ለገበሬዎቻችን፣ ለኢኮኖሚያችን እና ለኢትዮጵያ ነገ ስንል እንጨርሰዋለን ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክታቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም