የአየር ትራንስፖርት መጀመሩ የቦረና ብሔራዊ ፓርክ ጎብኚዎችን ቁጥር ያሳድጋል - ኢዜአ አማርኛ
የአየር ትራንስፖርት መጀመሩ የቦረና ብሔራዊ ፓርክ ጎብኚዎችን ቁጥር ያሳድጋል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2017 (ኢዜአ)፡- የኢትየጵያ አየር መንገድ ከፊታችን እሁድ ጀምሮ ወደ ያቤሎ በረራ መጀመሩ የቦረና ብሔራዊ ፓርክን ለሚጎበኙ ቱሪስቶች ከፍተኛ ሚና እንደሚያበረክት ተገለጸ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነሐሴ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ወደ ያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያ በሳምንት ሦስት በረራዎችን ለማድረግ የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቋል።
የአየር ትራንስፖርት መጀመሩ የጎብኚዎችን የመጓጓዣ አማራጭ በማስፋት ቁጥራቸውን እንደሚያሳድገውም የቦረና ብሔራዊ ፓርክ ዋርድ ንጉሴ ዋታ ለኢዜአ ተናግረዋል።
የጎብኚዎች ቁጥር ከፍ ሲልም የዞኑን ኢኮኖሚ፣ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነትና የፓርኩን እድገት ለማፋጠን እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
ወደ ፓርኩ የሚመጡ ጎብኚዎች እና የአካባቢው ማኅበረሰብ የአየር ትራንስፖርት እንዲኖር በተደጋጋሚ ሲጠይቁ እንደነበር አውስተው፤ ከፊታችን እሁድ ጀምሮ ጥያቄው በተግባር መመለሱን አመላክተዋል።
ቦረና ብሔራዊ ፓርክ ለጎረቤት ሀገራት በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቱ ከኬንያ እና ታንዛንያ የሚመጡ በርካታ ጎብኚዎች የሚጎበኙት መሆኑንም ጠቁመዋል።
በ2017 የበጀት ዓመት 1 ሺህ 331 ጎብኚዎች ፓርኩን መጎብኘታቸውን እና ከዚህ ውስጥ ከ75 በመቶ የሚልቁት የውጭ ሀገራት ዜጎች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
ወደ ቦረና ብሔራዊ ፓርክ ለመግባት አራት የመግቢያ በሮች እንዳሉ ጠቁመው፤ ጎብኝዎች በፓርኩ ለሚኖራቸው ቆይታም በቂ አገልግሎት እየቀረበ መሆኑን ነው ያረጋገጡት።