የወባ በሽታን ለመከላከል በአካባቢ ቁጥጥርና አጎበር ስርጭት ላይ በማተኮር የተጠናከረ ተግባር እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የወባ በሽታን ለመከላከል በአካባቢ ቁጥጥርና አጎበር ስርጭት ላይ በማተኮር የተጠናከረ ተግባር እየተከናወነ ነው

ወልዲያ ፤ ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፡-በሰሜን ወሎ ዞን የወባ በሽታን ለመከላከል በአካባቢ ቁጥጥርና አጎበር ስርጭት ላይ በማተኮር የተጠናከረ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ።
ከጤና ባለሙያዎች ባገኙት ትምሕርት የወባ በሽታ አምጪ ትንኝ የሚፈለፈልበትን ቦታ በመለየት እያዳፈኑና እያፀዱ እንደሚገኙ በዞኑ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የዞኑ ጤና መምሪያ ተወካይ አቶ ነጻነት ፋንታዬ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ከአየር ፀባይ መለዋወጥ ጋር ተያይዞ በዞኑ ከቆላማ ስፍራዎች ባሻገር በወይና ደጋ አካባቢዎችም የወባ በሽታ ምልክት እየታየ መጥቷል።
በዞኑ 12 ወረዳዎች የወባ በሽታ ተጋላጭ በመሆናቸው ቀድሞ የመከላከል ስራ አስፈላጊ መሆኑን ታምኖበት ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።
በዚህም የክረምቱ መውጣት ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የወባ በሽታ ከወዲሁ አስቀድሞ ለመከላከል ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ የሆነ 242 ሺሕ 515 ስኩየር ሜትር ቦታ የማፋሰስ፣ የማዳፈን፣ የጠረጋና የማፅዳት ስራዎችን ማከናወን መቻሉን አንስረድተዋል።
የበሽታው ይበልጥ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ደግሞ 82 ሺሕ 697 የአጎበር ስርጭት መከናወኑን ጠቅሰው፤ የመከላከሉ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
ከመከላከል ስራው ጎን ለጎንም የበሽታው ምልክት የሚታይባቸው የሕብረተሰብ ክፍሎችን ፈጥኖ ለማከም የመድሃኒት አቅርቦትና የጤና ተቋማት ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የጤና ባለሙያዎች ለሕብረተሰቡ ስለ ወባ በሽታ መንስኤ፣ መከላከያ መንገዶችና መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ ትምሕርት እየሰጡ ናቸው ብለዋል።
ሕብረተሰቡም የመከላከል ስራው ውጤታማ እንዲሆን አሁን እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዞኑ ሐብሩ ወረዳ የቁጥረ 8 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ይማም አያሌው በሰጡት አስተያየት፤ የወባ በሽታን ለመከላከል በአካባቢያቸው ረግረጋማ በታዎችን በማፋሰስ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላውም የሕብረተሰቡ ክፍል የማዳፈንና የጠረጋ ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሁሉም የቀበሌው ነዋሪ በተሰጠው ትምሕርት የወባ በሽታ አምጪ ትንኝ የምትፈለፈልበትን ቦታ እየለየ የማዳፈንና የማፅዳት ስራ እያከናወንን እንገኛለን ያሉት ደግሞ በጉባላፍቶ ወረዳ የገዶ በር ቀበሌ ነዋሪ መለሰ ሰጠኝ ናቸው።