አስም-የበርካቶች ሰቀቀን … - ኢዜአ አማርኛ
አስም-የበርካቶች ሰቀቀን …

በወቅትና የአየር ሁኔታ ሳይገደብ የበርካቶች ስቃይ የሆነውን አስም እንዴት ማከም ይቻላል…?
የድንገተኛ እና ጽኑ ህሙማን ሐኪም ዶክተር ፍጹም አሸብር ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ለአስም ስለሚያጋልጡ መንስኤዎች፣ ምልክቶች፣ መደረግ ስላለበት ጥንቃቄና ሕክምናው አብራርተዋል።
• አስም ምንድን ነው?
እንደ ዶክተር ፍጹም ገለጻ፤ አስም ለረጅም ጊዜ የሚኖር የመተንፈሻ አካላት ህመም ነው። የመተንፈሻ አካላት በቀላሉ፣ በተለያየ ሁኔታና መጠን መዘጋት ሲያጋጥም አስም ይባላል።
• የአስም ህመም ምልክቶች ምንድን ናቸው?
የትንፋሽ ማጠር፣ የደረት መጨናነቅ እና ሳል ከአስም ምልክቶች መካከል መሆናቸውን ያነሱት የሕክምና ባለሙያው፤ በአብዛኛው ምልክቶቹ በሌሊት ወይም በማለዳ እንደሚባባሱ ገልጸዋል።
• የአስም ዓይነቶች
1. የአለርጂ አስም፡- ይህ የአስም ዓይነት በአለርጂዎች የሚቀሰቀስ መሆኑን ገልጸው፤ ለምሳሌ አቧራ፣ የአበባ ዱቄት (ዘር) ብናኝ፣ የእንስሳት ፍግ ሽታዎች አጋላጭ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
2. አለርጂ ያልሆነ አስም፡- ይህ ደግሞ በኢንፌክሽን፣ በቀዝቃዛ አየር እንዲሁም በተበከለ አየር የሚነሳ የአስም ዓይነት መሆኑን ነው ያስረዱት።
3. በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ምክንያት የሚመጣ አስም፡- አካላዊ እንቅስቃሴ በሚደረግበት ወቅት እንዲሁም ከሥራ በኋላ የሚከሰት የአስም ዓይነት መሆኑን ያስረዳሉ።
4. ከሥራ ጋር የተያያዘ አስም፡- በሥራ ቦታ ተጋላጭነት ምክንያት የሚቀሰቀስ የአስም ህመም ዓይነት መሆኑን ገልጸዋል።
5. ከባድ የአስም በሽታ፡- ይህኛው የአስም ህመም ዓይነት ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እና ባብዛኛው ባዮሎጂካል ሕክምናን የሚፈልግ መሆኑን አስረድተዋል።
• ለአስም ህመም አጋላጭ ወይም ለህመሙ መባባስ መንስኤዎቹ ምንድን ናቸው?
አለርጂዎች (የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን፣ የአየር ብክለት፣ ጭስ)፤
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ፣ ጭንቀት እንዲሁም የጄኔቲክ ቅድመ-ዝንባሌ ለአስም ህመም ከሚያጋልጡ እና ህመሙን ከሚያባብሱ ምክንያቶች መካከል መሆናቸውን ዶክተር ፍፁም ገልጸዋል።
• አስም ያለባቸው ሰዎች ምን ይነት ጥንቃቄ ያድርጉ?
ከአቧራ፣ ጭስ፣ አለርጂዎች መራቅና መጠንቀቅ፤
በኢንፍሉዌንዛ እና በኒሞኮካል ክትባቶች ወቅታዊ ክትባቶችን መውሰድ፤
በቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ ወቅት ሙቀት የሚሰጡ ልብሶችን መልበስ፤
ጥሩ እንቅልፍ መተኛት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ የተመጣጠነ አመጋገብን ማዘውተር እና መሰል ተግባራት የአስም ህመም እንዳይባባስ ያግዛሉ ብለዋል ባለሙያው።
• ሕክምናውስ ምንድን ነው?
የአስም ህመም የማስታገሻ እና የመቆጣጠሪያ (የረዥም ጊዜ) ሕክምናዎች እንዳሉት ያስታወቁት ባለሙያው እንደ ህመሙ ሁኔታ ስለሚወሰን ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ እንደሚገባ መክረዋል።
በተለይም ምልክቶቹ በተባባሱበት ወቅት ከፍተኛ የአየር ትቦ መዘጋት ደረጃ ላይ እንዳይደርስ በጊዜ ሕክምናውን ማግኘት አስፈላጊ መሆኑን በአጽንኦት አንስተዋል።