ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን የህዳሴ ግድብን በህብረት በማሳካት አዲስ የድል ምዕራፍ ከፍተዋል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፡- በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በራስ አቅምና በተባበረ ጥረታቸው በማሳካት አዲስ የድል ምዕራፍ መክፈታቸውን የግድቡ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።  

የጽህፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የግድቡ ሠራተኞች ፈታኙን የጉባ በረሃ ሙቀት ተቋቁመው ቀን ከሌሊት በመሥራት ደማቅ አሻራቸውን ማሳረፋቸውንም አንስተዋል።

የዚህ ዘመን ትውልድ በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በጉልበት እንዲሁም የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ግድቡን ለፍጻሜ በማብቃት የዓባይን ወንዝ ለልማት የማዋል የዘመናት ጥያቄን መልሷል ነው ያሉት።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የህብረት፣ የቁርጠኝነትና የአርበኝነት ውጤት መሆኑን ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያ ለጫናዎች ሸብረክ ሳትል ግድቡን በማጠናቀቅ ለምረቃ ማብቃቷን ገልጸዋል።

ግድቡ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ማሳካት፣ ድህነትን ማስወገድና የመዳረሻ ግቧን ማሳካት እንደምትችል ለዓለም ያሳያ ነው ብለዋል።

ስኬቱ ለሀገራችን አዲስ ታሪክ የተሰራበትና ትውልድ ለዘመናት የሚያወሳው አኩሪ ተጋድሎ መሆኑን ተናግረዋል።

በጠንካራ አንድነት መነሳት የትኛውንም ዓይነት ግብ ለማሳካት እንደሚቻል ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፤ ስኬቱ ለመጪው ትውልድና ለሌሎች ሀገራት ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ከድህነት ለመላቀቅ ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳዩበት ትልቅ የሀገር ሀብት መሆኑንም ገልጸዋል።

መላው ህዝብ፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ዘርፈ ብዙ ድጋፍ በማድረግ ግድቡ ተጠናቆ ለምረቃ እንዲበቃ ላደረጉት ጉልህ አስተዋጽኦ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
 

የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፈዬራ ዲንሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው ግድቡ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ልዑላዊነቷን ለማረጋገጥ ለጀመረችው ጉዞ ጉልህ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በቀጣይ ትላልቅ ስራዎችን ለማከናወን መነሳሳትን በመፍጠር ትልቅ አቅም እንደሚሆንም ገልጸዋል።

የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ካሳ ሻውል (ዶ/ር) እንዳሉት፥ የግድቡ በስኬት መጠናቀቅ በቀጣይ ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደምንችል ያሳየ ነው።
 

ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንድ የሀገራቸውን ፈጣን ዕድገት እንደሚያሳኩ በተጨባጭ የተረጋገጠበት ነው ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም