በሲዳማ ክልል የአንድ ማዕከል የመሶብ አገልግሎት ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ

ሀዋሳ፤ ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋና ዘመናዊ ለማድረግ የአንድ ማዕከል የመሶብ አገልግሎት ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

በክልሉ ያለውን እምቅ ሃብት በማልማት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

በሲዳማ ክልል የልማት፣ የአገልግሎት አሰጣጥና አጠቃላይ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችንና የተገኙ ውጤቶችን በተመለከተ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በማብራሪያቸው ከለውጡ በኋላ በሲዳማ ክልል በሁሉም መስኮች የሚታዩና የሚጨበጡ ውጤቶች መመዝገባቸውንና ለህዝቡ የልማትና የአገልግሎት ፍላጎቶች ምላሽ የሚሰጡ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውንም አንስተዋል።

በተለይም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት፣ ፈጣንና ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ለመዘርጋት በልዩ ትኩረትና በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊና ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት መዘርጋት የግድ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋና ዘመናዊ ለማድረግ የአንድ ማዕከል የመሶብ አገልግሎት ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም የሕንጻ፣ የሰው ሀይልና መሰል ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን አመልክተዋል።

በከተማም ይሁን በገጠር ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ማሳካት እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ዝግጁነት ስለመኖሩም አስረድተዋል።

የህዝብን ተጠቃሚነት የማረጋገጥና ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የመስጠት ጉዳይ በመንግስት ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ለመንግስት ሰራተኛው የደመወዝ ጭማሬ የማድረግ ውሳኔም የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል።

መንግስት የሚያደርገውን የደመወዝ ጭማሬ ተከትሎ የዋጋ ንረትና ያልተገባ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ በሚሞክሩ አካላት ላይም ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ ገልጸው፤ ለዚህም ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ወደስራ ተገብቷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም