በገጠር ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የማዳረሱ ተግባር የሕብረተሰቡን ችግር እያቃለለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በገጠር ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የማዳረሱ ተግባር የሕብረተሰቡን ችግር እያቃለለ ነው
ባሕርዳር ፤ነሐሴ 21/2017 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የገጠር ቀበሌዎች እየተከናወነ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የማዳረስ ተግባር የሕብረተሰቡን ችግር እያቃለለ መሆኑ ተገለጸ።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአማራ ሪጅን ሀገር አቀፍ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም ኃላፊ አቶ ኪሩቤል ከፍያለው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በሀገር አቀፍ የኤሌክትሪክ ፕሮግራም በገጠር ቀበሌዎች የሕብረተሰቡን የኃይል አቅርቦት ችግር ለማቃለል በትኩረት እየተሰራ ነው።
በ2017 የበጀት ዓመት በ34 የገጠር ቀበሌዎች የዝቅተኛና መካከለኛ የኤሌክትሪክ መስመር በመዘርጋት 60 ሺህ የሚጠጉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አውስተዋል።
በዚህም የሕብረተሰቡን የዘርፉ አገልግሎት ጥያቄ በመመለስ ችግሩን ከማቃለሉም በሻገር ዘመናዊ አኗኗርን እየተለማመደ እንዲመጣ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።
ተግባሩን በመቀጠልም በተያዘው የበጀት ዓመት በክልሉ 23 የገጠር ቀበሌዎችን በፕሮግራሙ የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን አስረድተዋል።
ይህም የዝቅተኛና መካከለኛ መስመር በመዘርጋትና 14 ሺህ 227 ቆጣሪዎችን በማገናኘት 64 ሺህ የሚጠጉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚሆኑም አስታውቀዋል።
በክልሉ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ለገጠሩ ማሕበረሰብ ተደራሽ በማድረጉ ሂደት ጊዜያዊ የስራ ዕድል እንደሚፈጠር አመልክተዋል።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጣቁሳ ወረዳ የሮቢት አይብጋ ቀበሌ አርሶ አደር ደጉ አድማስ በሰጡት አስተያየት፤ ዘንድሮ በቀበሌያቸው የኤሌክትሪክ መብራት በመግባቱ ዘመናዊ አኗኗርን እንዲለምዱ እንዳስቻላቸውና ልጆቻቸው በፈለጉት ሰዓት ተነስተው እንዲያነቡ እንደሚያበረታቱም ጠቁመዋል።
ካለፈው ሚያዚያ ወር ጀምሮ የኤሌክትክ መብራት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በባሕርዳር ከተማ አስተዳደር የይጋንዳ ተክለሃይማኖት ቀበሌ አርሶ አደር ጊዜው ጌታሁን ናቸው።
ይህም በትምህርት ላይ የሚገኙ ልጆቻቸው ከኩራዝ ጭስ ተላቀው ሌሊት በፈለጉት ሰዓት ተነስተው እንዲያጠኑና የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ እንዳገዛቸው ተናግረዋል።