የአፍሪካ ህብረት ሴቶች በሰላም ግንባታ ያላቸውን ሚና ለማሳደግ በልዩ ትኩረት ይሰራል- መሐሙድ አሊ ዩሱፍ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ህብረት ሴቶች በሰላም ግንባታ ያላቸውን ሚና ለማሳደግ በልዩ ትኩረት ይሰራል- መሐሙድ አሊ ዩሱፍ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2017(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ህብረት ሴቶች በአህጉራዊ የሰላም ግንባታ እና መረጋጋት ያላቸውን ሚና የበለጠ ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ገለጹ።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ አዲስ ከተሾሙት የህብረቱ የሴቶች፣ የሰላም እና ደህንነት ልዩ ልዑክ አምባሳደር ላይቤራታ ሙላሙላ ጋር በአዲስ አበባ የመጀመሪያ ስትራቴጂካዊ ውይይት አድርገዋል።
ሊቀ መንበሩ በአፍሪካ ህብረት የግጭት አፈታት ጥረቶች ውስጥ የሴቶች መሪነት እና ጥበቃ ዋንኛ የትኩረት ማዕከል መሆን እንደሚገባው አመልክተዋል።
በተለይም ሴቶች ግጭት እና ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ጉዳዩ የተለየ ትኩረት እንደሚያሻው ገልጸዋል።
የአምባሳደር ላይቤራታ የስራ ኃላፊነት እንደ አጀንዳ 2036 እና የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ደህንነት መዋቅር (APSA) ካሉ የረጅም ጊዜ ግቦች ጋር ከመተሳሰሩ ባሻገር ህብረቱ የሚመራቸውን ድርድሮችና የሰላም ሂደቶች ላይ ከሴት አሸማጋዮችና የስርዓተ ጾታ እይታዎች ጋር የማቆራኘት ግብ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
ከንግግር በመሻገር ለሴቶች ጥበቃ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ የሰላምና ደህንነት ጉዳይ ውሳኔ ሰጪ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ሀገር በቀል ሲቪክ ማህበራት በሴቶች ጉዳይ ጠንካራ ትብብር መፍጠርና አህጉራዊ የተጠያቂነት ስርዓትን የበለጠ ማረጋገጥ እንደሚገባ አመልክተዋል።
በሴቶች ለሚመሩ ኢኒሼቲቮች ዘላቂ የፋይናንስ አቅርቦት ሊኖር ይገባል ያሉት ሊቀ መንበሩ በዚህ ረገድ አፍሪካ ህብረት ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ሙሉ ድጋፉን እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል።
የአፍሪካ ህብረት ሴቶች በሰላም ግንባታ ያላቸውን ሚና ለማሳደግ አበክሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የአፍሪካ ህብረት የሴቶች፣ የሰላም እና ደህንነት ልዩ ልዑክ አምባሳደር ላይቤራታ ሙላሙላ በመጀመሪያ ዓመት የስልጣን ዘመናቸው ለሴቶች መብት መከበር በጽኑ መሟገት፣ የሴቶች የፖለቲካ መሪነት ማሳደግ እና በስርዓተ ጾታ የሚጨበጡ ውጤቶችን ማምጣት ላይ አተኩረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ውይይቱ የአፍሪካ ህብረት አህጉራዊ እና የአባል ሀገራትን ቃል ኪዳኖች ወደ ሚጨበጥ ውጤት በመቀየር ሴቶችና ልጃ ገረዶች በአህጉሪቷ የሰላምና ደህንነት ሂደቶች ያላቸውን ሚና በማሳደግ ለውጥ ለማምጣት ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ መግለጹን ኢዜአ ከህብረቱ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።