ጉባኤው ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ልምዷን ለሀገራት የምታጋራበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ጉባኤው ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ልምዷን ለሀገራት የምታጋራበት ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 21/2017(ኢዜአ)፦ ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እያከናወነች ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ልምዷን ለሀገራት የምታጋራበት መሆኑ ተገለፀ።
ኢትዮጵያ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ታስተናግዳለች።
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ስራ አስፈፃሚና የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ብሄራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ ጸሐፊ ፋኖሴ መኮንን እንዳሉት ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በርካታ ስራዎችን እያከናወነች ትገኛለች።
ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ አንፃር ህብረተሰቡን በማስተባበር በተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ከ33 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት እንዲያገግም ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።
በክረምቱ መርሃ ግብር በስነ-ህይወታዊ አፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ይህንን የማጠናከር ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በዚህ ረገድ በዋናነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ያስቻለ መሆኑን ጠቁመው፤ የደረቁ የውሃ አካላት መልሰው እንዲያገግሙ ማድረጉን ተናግረዋል።
በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነትና ስትራቴጂክ አጋርነት መሪ ስራ አስፈፃሚ መንሱር ደሴ፥ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችሉ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች እየተተገበሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት የአረንጓዴ አሻራ፣ ታዳሽ ኃይል፣ ትራንስፖርትና ሌሎችም ስራዎች ተጨባጭ ውጤት የመጣባቸው የአረንጓዴ ልማት ዘርፎች ናቸው ብለዋል።
ኃላፊዎቹ አክለውም ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ እያከናወነች ያለችው ተግባር ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን በጋራ የመልማት ትብብርን እያጠናከረ እንደሚገኝ አንስተዋል።
ለሌሎች የአፍሪካ እና የዓለም ሀገራትም ትልቅ ተሞክሮ መሆኑን ጠቅሰው፥ ጉባኤው አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ እያከናወነች ያለችውን ተግባር ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የምታሳይበት መሆኑን ተናግረዋል።