ኢትዮጵያ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመደገፍ ወንጀልን ለመከላከል በትኩረት እየሰራች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመደገፍ ወንጀልን ለመከላከል በትኩረት እየሰራች ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 21/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መንግሥት ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመደገፍ ወንጀልን ለመከላከል በትኩረት እየሰራ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር እና ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመደገፍ ወንጀልን መከላከል ብሔራዊ ኮሚቴ ሊቀ መንበር ዓለምፀሐይ ጳውሎስ ገለጹ፡፡
የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን 50ኛው የከፍተኛ ባለሙያዎች፣ 25ኛው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ እና ስምንተኛው የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የውይይት ፎረም በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን እየተካሄደ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር እና የጸረ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ ወንጀልን መከላከል ኮሚቴ ሊቀ መንበር ዓለምፀሐይ ጳውሎስ በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍን ለመከላከል በቡድኑ ሀገራት መካከል ጠንካራ ትብብር ሊኖር ይገባል።
ስብሰባው በጋራ ከመምከር ባለፈ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመቆጣጠር የፋይናንስ ስርዓቱን ለማዘመንና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የጋራ ቁርጠኝነት መኖሩ የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።
የቡድኑ አባል ሀገራት በችግሮች ላይ በመምከር የጋራ መፍትሄ ማበጀት እንዳለባቸው በመጥቀስ፣ በሀገራት መካከል ትብብር፣ ተጠያቂነትና የቴክኒክ ልህቀት ሊኖር ይገባል ብለዋል።
እነዚህን ቀጣናዊ ችግሮች ለመከላከል የጋራ ተቋማትንና ቀጣናዊ ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባም ገልጸዋል።
የከፍተኛ ባለሙያዎች ግብረ ኃይል ለምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን የጀርባ አጥንት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመደገፍ ወንጀልን መከላከል በመንግሥት ትኩረት የተሰጠው መሆኑን በመግለፅ፣ ለዚህም 23 ተቋማትን የያዘ ብሔራዊ ኮሚቴ መኖሩን ተናግረዋል፡፡
ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመደገፍ ወንጀልን መከላከል ብሔራዊ አጀንዳ ሆኖ እየተሰራበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሀገራዊ ሪፎርሙ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመደገፍ ወንጀልን የመከላከል ሥራን ለማጎልበት እንደ ፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ያሉ ተቋማት እንዲጠናከሩ መደረጉን ተናግረዋል።
ለህግ ማስከበርና ለተጠያቂነት ስርዓት ትኩረት መሰጠቱንም አስታውቀዋል።
በመርሀ ግብሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንክ ቁጥጥር ዳይሬክተር እና የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን የከፍተኛ ባለሙያዎች ግብረ ሀይል ሊቀ መንበር ፍሬዘር አያሌው፣ የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን ፋይክል ዚታ፣ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሙሉቀን አማረን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ የዘርፉ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።