በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች ይጠናከራሉ - ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)

ሆሳዕና ፤ነሐሴ 21/2017 (ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለፁ፡፡

"ሰላምን ማፅናት ለክልሉ ሁለንተናዊ ብልፅግና" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የክልሉ ፀጥታ ምክር ቤት የምክክር መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል፡፡ 


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት በክልሉ ዘላቂ ሰላምን በማጽናት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡

ለዚህም የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ትግበራን የማስፋትና የተጠናከረ የህግ ማስከበር ስራ ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸዋል፡፡ 

ሰላምን ማስጠበቅና ማፅናት በክልሉ እየተመዘገበ ያለውን ፈጣን እድገት ለማስቀጠል ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ የሀይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የትምህርት ተቋማት በሰላም ግንባታ ላይ አበክረው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በዚህም በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ዘላቂ ሰላምን በማፅናት የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።


 

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ በበኩላቸው በክልሉ የፀጥታ መዋቅሩ ከህዝቡ ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም  ሰላምን በዘላቂነት ለማጽናት የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡

የክልሉ ፀጥታ ምክር ቤት አባል ወይዘሮ ጀሚላ ኢብራሂም፣ የሴቶችን አደረጃጀት በመጠቀም ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥና እድገትን ለማስቀጠል መስራት ይገባል ብለዋል።

ሌላው የምክር ቤቱ አባል ወጣት ነስሩ ኡመር በበኩሉ በአካባቢው የህዝብ ለህዝብ ትስስር በማጠናከር ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እየሰራን ነው ብሏል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ በብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዞን አስተዳዳሪዎች፣ የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት አባላት፣ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም