ኢትዮጵያ ቀጣናዊና አህጉራዊ ትስስርን አጠናክራ ቀጥላለች - ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ቀጣናዊና አህጉራዊ ትስስርን አጠናክራ ቀጥላለች - ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ቀጣናዊና አህጉራዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ ተግባራትን አጠናክራ መቀጠሏን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ።
15ኛው የምስራቅ አፍሪካ የኮሙኒኬሽን ማህበር ጉባኤ “ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ለአፍሪካ ውህደት" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት አፍሪካ በአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063፣ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና እና በተለያዩ አህጉራዊ ውጥኖች አማካይነት በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ የትስስር ጉዞ ላይ ትገኛለች።
ቀጣናዊ እና አህጉራዊ ውህደትን እውን ለማድረግ የመሰረተ ልማት ትስስርን፣ ቀጣናዊ ትብብርን በማጠናከር እና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ጥልቅ የባህል ልውውጥ ማድረግ ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የሚዲና ኮሙኒኬሽን ሥራዎችም የጋራ ትርክት በመገንባት፣ የጋራ ማንነትን እና እጣ ፈንታን በማሳየት የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው አንስተው የሚሰሩ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የጋራ ማንነቶችን ለማጉላት፣ በሀገሮች መካከል ትብብርን ለማጠናከር ጽኑ አቋም እንዳለው ገልጸው፥ ለዚህም በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ቀጣናዊና አህጉራዊ ትስስርን ለማጠናከር እየሰራች ነው ያሉት ሚኒስትሩ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋር በመሰረተ ልማት ትስስር፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እና ኢኮኖሚያዊ ትብብር ቀጣናዊ ትስስርን እያፋጠነው ነው ብለዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም የምስራቅ አፍሪካ የኮሙኒኬሽን ማህበር የሚዲያ እና የኮሙኒኬሽን ኢንዱስትሪ ችግሮችን ለመፍታት የመፍትሔ ሀሳቦችን በማቅረብ የበለጠ ጠንካራ ሚና መጫወት እንዳለበት አስረድተዋል።
የዘርፉ ምሁራን የአፍሪካን ውህደት ለማጠናከር እና የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ የመደመር መንገዶችን በማሳየት ጥረታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸውም እንዲሁ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው የበለፀገች አፍሪካን ለማረጋገጥ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ሚና ወሳኝ ነው ብለዋል።
ጉባኤው የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ምሁራን ዴሞክራሲን ለማጎልበትና ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር የሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ለመምከርና የመፍትሔ ሀሳቦችን ለማፍለቅ ምቹ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን የአፍሪካን ትርክት በመቅረጽ፣ ትብብርን በማጎልበት እና እድገትን በማምጣት ረገድ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው ያሉት ደግሞ የምስራቅ አፍሪካ የኮሙኒኬሽን ማህበር ፕሬዚዳንት ማርጋሬት ጁኮ (ፕ/ር) ናቸው።
ጉባኤው ምሁራን በዘርፉ ያሉ ጉዳዮች ላይ በመምከር የበለፀገች አፍሪካን ለመፍጠር ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።