የቴምር ፌስቲቫሉ የኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነት የማረጋገጥ ግብ ለማሳካት የላቀ እገዛ አለው - ኢዜአ አማርኛ
የቴምር ፌስቲቫሉ የኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነት የማረጋገጥ ግብ ለማሳካት የላቀ እገዛ አለው
ሠመራ፤ ነሐሴ 21/2017(ኢዜአ)፡- በአፋር ክልል የተካሄደው የቴምር ፌስቲቫል ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የያዘችውን ግብ ለማሳካት ለሚከናወነው ሥራ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተመለከተ።
የመጀመሪያው ዓለም ዓቀፍ የቴምር ፌስቲቫል በሁለተኛ ቀን ውሎው ላይ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ተመራማሪዎች በተገኙበት በፓናል ውይይት ተካሄዷል።
በዚሁ ፌስቲቫል ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ኢፋ ሙለታ (ዶ/ር) እንዳሉት ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ያስቀመጠችው ግብ ከስኬት እንዲደርስ የቴምር ልማት ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው።
ፌስቲቫሉ ዘርፉን ለማስፋት እና አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።
በተለይም በቆላማ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያለው መሬት ለተክሉ አመቺ በመሆኑ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርታማነቱን ማሳደግ እንዲቻልና የኢኮኖሚ ጠቀሜታን ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
በተለይም በዘርፉ የተሰማሩ አልሚዎችና ባለድርሻ አካላት የቴክኖሎጂ ሽግግሩን በማስፋት ሂደት እና የስራ ዕድል ለወጣቶች ከመፍጠር አኳያ እገዛ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዮት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ድሪባ ገለቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው ፌስቲቫሉ የቴምር ምርታማነትን ለማሳደግ ቴክኖሎጂ፣ ኢኖቬሽንና የተማረ የሰው ሐይል የተገናኙበት መሆኑን ተናግረዋል።
በቴምር ልማቱ የተሰማሩ አርሶ አደሮችና ኢንቨስተሮችን ከማበረታታት ባለፈ ዘርፉ በፖሊሲና ስትራቴጂ መደገፍ እንዳለበት ጠቁመዋል።
እሰካሁን ድረስ በአገር አቀፍ ደረጃ በተደረገ ምርምር ሁለት ሺህ የሚሆኑ የቴምር ዛፎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ከዚህም እስከ ስምንት ሺህ ኩንታል ቴምር እንደሚመረት ገልፀዋል።
በቀጣይነት በእነዚህ ቆላማ አካባቢዎች በትኩረት ከተሰራ ምርቱን ማሳደግ እንደሚቻል ነው ያብራሩት።
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የወረር ግብርና ማዕከል ተመራማሪ አቶ ይታገሱ ኩማ እንዳሉት በአፋር ክልል በወረር፣ አፋምቦና አይሳኢታ አካባቢዎች 14 ዝርያዎች ምርታቸውን የመገምገምና የማስፀደቅ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ምርታቸው ከጸደቀ በኋላ በግብርና ዝርያ አስለቃቂ ኮሚቴ ቀርቦ ለአርሶ አደሩም የሚለቀቅ መሆኑን ገልፀዋል።
በሠመራ ከተማ እየተካሄደ ያለው ዓለም ዓቀፉ የቴምር ፌስቲቫል እንደቀጠለ ነው።