የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎትን ይበልጥ የሚያዘምን የቴክኖሎጂ ሥርዓት በቅርቡ ይተገበራል - ኤጀንሲው - ኢዜአ አማርኛ
የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎትን ይበልጥ የሚያዘምን የቴክኖሎጂ ሥርዓት በቅርቡ ይተገበራል - ኤጀንሲው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 21/2017(ኢዜአ)፦ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎትን ይበልጥ የሚያዘምን የቴክኖሎጂ ሥርዓት በቅርቡ እንደሚተገበር የአዲስ አበባ ሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ አስታወቀ።
ከሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት መካከል የነዋሪነት አዲስ መታወቂያ ማውጣትና ማደስ፣ የልደት ፣ የሞት፣ የጋብቻ፣ የፍቺ እንዲሁም የጉዲፈቻ ሰርተፍኬት ማግኘት ይጠቀሳሉ፡፡
የአዲስ አበባ ሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ንጉሴ ለኢዜአ እንደገለጹት ተቋሙ አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ባካሄደው ሪፎርም ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል።
ሪፎርሙ በዋናነት በዘርፉ የነበረውን ብልሹ አሰራር መቅረፍ፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ፈጣን አሰራርን ተግባራዊ ማድረግ፣ አደረጃጀቶችን መቀየርና ምቹ የስራ ሁኔታ መፍጠር ላይ ትኩረት ማድረጉን ጠቅሰዋል።
ኤጀንሲው በከተማዋ በ11 ቱም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ 119 ወረዳዎች የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ዲጂታላይዝ በማድረግ ለነዋሪዎች ፈጣንና ቀልጣፋ መስተንግዶ ለመስጠት በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የተፈጠረው አሰራር ህገ ወጥ አካሄድን ከማስቀረቱ ባለፈ ቀደም ሲል በተቋሙ ይታይ የነበረውን የሃሰተኛ ሰነድ ዝግጅትና ስርጭት ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ተጠያቂነትን ለማስፈን ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ነው ያሉት።
በቴክኖሎጂ የታገዘው ፍትሃዊ፣ ቀልጣፋና ዘመናዊ አሰራር ዜጎች ሳይጉላሉ የሚፈልጉትን አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻሉንም ተናግረዋል።
በዘርፉ የሚሰጡ አገልግሎቶች በርካታ በመሆናቸው የማህበረሰቡን ፍላጎት በፍጥነት በመመለስ ረገድ ውስንነቶች መኖራቸውን ሃላፊው ጠቅሰዋል።
በመሆኑም በዘርፉ የተገኙ ውጤቶችን ለማጠናከርና ጉድለቶቹን ለመሙላት አሰራሩን ይበልጥ ማዘመን አስፈላጊ መሆኑን ነው ያስታወቁት።
ለዚህ የሚረዳ ዘመናዊና ዜጎች በቀላሉ የሚገለገሉበት ቴክኖሎጂ መልማቱን በመጠቆም ቴክኖሎጂው ተገልጋዮች የሚፈልጉትን አገልግሎት ባሉበት ቦታ ሆነው የሚያገኙበትን አሰራር የሚዘረጋና በዘርፉ የሚሰጠውን የዲጂታል አገልግሎት ከፍ የሚያደርግ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።
የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ያገኙ ተገልጋዮች በበኩላቸው በዲጂታል የታገዘ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋቱ ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት እንድናገኝ አስችሎናል ብለዋል።
በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት የልደት ካርድ ዲጂታል ለማድረግ የመጣችው ወጣት ዮርዳኖስ ኤርሚያስ አገልግሎት አሰጣጡ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ በመሆኑ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዳገኝ ረድቶኛል ስትል ገልጻለች።
በዚሁ ወረዳ የነዋሪነት ማረጋገጫ ሰነድ ለማውጣት የመጣው ወጣት ከተማ መርጊያ በበኩሉ ቀደም ሲል በወረዳው ይሰጥ የነበረው አገልግሎት የተንዛዛና የአሰራር ስርዓት ያልተበጀለት እንደነበር አስታውሷል።
ወረዳው አሁን ላይ አገልግሎት አሰጣጡን የሚያሻሽሉ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ በማዋሉ ቀልጣፋና ፍትሃዊ መስተግዶ ለማግኘት አንዳስቻላቸው ነዋሪዎቹ አስታወቀዋል፡፡
በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ መታወቂያ ለማሳደስ የመጡት ወይዘሮ አልማዝ ወልደሰንበት እና አቶ ኑሩ አብዱራህማን የጽህፈት ቤቱ ሙያተኞቸ ያደረጉላቸው ትብብር የሚያስመሰግን መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ነዋሪዎቹ በወረዳው እየተሰጠ ያለው አገልግሎት ቀጣይነት እንዲኖረው አንስተው፤ የአሰራሩ መሻሻል ቀደም ሲል የነበረውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የመለሰ በመሆኑ ተግባሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።