በምስራቅ ቦረና ዞን በግንባታ ላይ የሚገኘው የመስኖ ፕሮጀክት አፈጻጸም 73 በመቶ ደረሰ - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ቦረና ዞን በግንባታ ላይ የሚገኘው የመስኖ ፕሮጀክት አፈጻጸም 73 በመቶ ደረሰ

ነገሌ ቦረና ፤ ነሐሴ 21/2017(ኢዜአ)፦በምስራቅ ቦረና ዞን በ240 ሚሊዮን ብር በግንባታ ላይ የሚገኘው የመስኖ ፕሮጀክት አፈጻጸም 73 በመቶ መድረሱን የዞኑ መስኖና አርብቶ አደር ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
ምስራቅ ቦረና ዞን አብዛኞቹ ወረዳዎች በድርቅ የሚጠቁ፣ ዝናብ አጠርና በስፋት የእንስሳት እርባታ የሚካሄድባቸው ሲሆን የክልሉ መንግስትም 'ፊና' በተሰኘ ፕሮጀክት ዞኑን ጨምሮ በክልሉ ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች የመስኖ ግድብ ግንባታዎችን እያከናወነ ይገኛል።
በ'ፊና' ፕሮጀክትም በቆላማ አካባቢ ከእንስሳት እርባታ ጎን ለጎን በመስኖ ልማት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥን ታሳቢ ያደረገ የመስኖ መሰረተ ልማት ተቋማት ግንባታ እና ዝርጋታ እየተከናወነ መሆኑም ይታወቃል።
በምስራቅ ቦረና ዞን መስኖና አርብቶ አደር ጽህፈት ቤት የዲዛይንና ቁጥጥር ቡድን መሪ ኢንጂነር ተስፋሁነኝ ዳንኤል እንደገለጹት የመስኖ ፕሮጀክቱ እየተገነባ ያለው በዞኑ ሊበን ወረዳ ውስጥ ነው፡፡
ፕሮጀክቱ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የዝናብ ውሀ በመያዝ ከ65 ሄክታር በላይ መሬት የማልማት አቅም እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ጎን ለጎን 130 አባወራዎችን በመስኖ ልማት ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን ለቤት እንስሳትም ለመጠጥነት የሚያገለግል መሆኑን ተናግረዋል።
በግንባታ ላይ የሚገኘው የመስኖ ግድቡ በዚህ ወቅት አፈጻጸሙ 73 በመቶ ላይ መድረሱን ገልጸው ለመስኖ ፕሮጀክቱ ግንባታ ማስፈጸሚያ ከ249 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን ገልፀዋል፡፡
በዞኑ ጎሮዶላ እና ጉሚ ኤልደሎ ወረዳዎችም የተጀመሩ አዳዲስ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑን ገልፀው በዞኑ በግንባታ ላይ ካሉ የመስኖ ፕሮጀክቶች መካከል አብዛኞቹን በ2018 ዓ.ም በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።