ከ17 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች እየተከፋፈለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከ17 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች እየተከፋፈለ ነው
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 21/2017 (ኢዜአ):- በ2017/18 የምርት ዘመን እስከ አሁን ወደ ሀገር ውስጥ የገባው ከ17 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ዳፕ እና ዩሪያ ማዳበሪያ ለአርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች እየተከፋፈለ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
ኮርፖሬሽኑ ለምርት ዘመኑ ከውጭ ከሚገዛው 24 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ እስከ ነሐሴ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ 18 ሚሊዮን 962 ሺህ 484 ኩንታል ጂቡቲ ወደብ መድረሱን የተቋሙ የኮሙኒኬሽን እና ማኅበራዊ ኃላፊነት ሥራ አመራር ሥራ አስኪያጅ አቶ ጋሻው አይችሉህም ለኢዜአ ገልጸዋል።
ከዚህ ውስጥ 17 ሚሊዮን 507 ሺህ 432 ኩንታል ወይም 92 ነጥብ 3 በመቶው ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዞ በኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካይነት ለአርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች እየተከፋፈለ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ወደብ ላይ የሚገኘውን 1 ሚሊዮን 455 ሺህ 52 ኩንታል ቀሪ ማዳበሪያ በጭነት ተሽከርካሪዎችና በባቡር ፉርጎዎች ከዛሬ ጀምሮ ወደ ሀገር ውስጥ የማጓጓዙ ሥራ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በተያያዘም ከነሐሴ 21 ቀን ጀምሮ እስከ መስከረም 13/2018 ዓ.ም ድረስ ባሉት ቀናት 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ተጨማሪ ማዳበሪያ (2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ዩሪያ እና 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ዳፕ) በሰባት መርከቦች ጂቡቲ ወደብ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው አቶ ጋሻው የገለጹት።
የግብርና ሚኒስቴር በየዓመቱ እያጠና በሚያቀርበው የሀገሪቱ የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት መሰረት የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከተቋቋመበት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ዓለም አቀፍ ጨረታ እያወጣ የማዳበሪያ ግዥ በመፈጸም ላይ እንደሚገኝ የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።