ዘይት እና ዱቄትን በንጥረ ነገር በማበልፀግ የህብረተሰቡን ጤና የመጠበቅ ስራ በቅንጅት እየተሰራ ነው

አዳማ፤ ነሐሴ 21/2017(ኢዜአ)፦የምግብ ዘይት እና የስንዴ ዱቄትን በንጥረ ነገር በማበልፀግ የህብረተሰቡን ጤና የመጠበቅ ስራ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስቴር ገለፀ።

ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር በመተባበር የምግብ ዘይትና የስንዴ ዱቄትን በንጥረ ነገር ለማበልፀግ የተዘጋጁ አስገዳጅ ደረጃዎችን ወደ ተግባር ለማስገባት ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ መክሯል።


 

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬ ህይወት አበበ በመድረኩ እንደገለፁት፤ እንደ አገር ስርዓተ ምግብን እውን ለማድረግ እየተሰራ ነው።

በኢትዮጵያ 39 በመቶ የሚሆኑ ህፃናት የመቀጨጭና የመቀንጨር ችግር እንደሚታይባቸው ተናግረዋል።

ችግሩን ለመቅረፍም ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ በተጓዳኝ የስነ ምግብ ስርዓቱን ለማረጋገጥ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በተጨማሪም በጨው ላይ አዮዲን የመጨመር ስራ እንዲሁም የምግብ ዘይትና የስንዴ ዱቄትን በንጥረ ነገሮች እንዲበለፅጉ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዘርፉ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎችም የምግብ ማበልፀግ መርሃ ግብር ህግና አሰራሩን ተከትለው እንዲያመርቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው ብለዋል።

ለዚህም አመቺ የህግ ማዕቀፎችና አሰራሮች ተበጅተው አስገዳጅ የምግብ ዘይትና የስንዴ ዱቄት ማበልፀግ ደረጃዎች ተግባራዊ እንደሚደረጉም ተናግረዋል።

ጠንካራ የክትትል፤ ቁጥጥርና ድጋፍ ስራ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት የዜጎችን ጤና መጠበቅ አለብን ነው ያሉት ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ በበኩላቸው የምግብ ማበልፀግ ፕሮግራም ጤናማ ማህበረሰብን ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ብለዋል።


 

የበለፀገ ምግብ እጥረት በህፃናት የአእምሮ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል ያሉት አቶ ታረቀኝ ለመቀንጨርና መቀጨጭም መንስኤ ነው ብለዋል።

የጨው፣ የስንዴ ዱቄትና የምግብ ዘይት ማበልፀግ አስገዳጅ ደረጃዎች ትግበራን ከ2018 ዓ.ም ጀምሮ በዘርፉ አምራች ኢንዱስትሪዎች ተግባራዊ ማድረግ ይጀመራል ብለዋል።

መንግስት ስራውን ለማገዝ የሚያስችሉ ማሽነሪዎችን በማቅረብ የነበሩ የአሰራርና የህግ ክፍተቶችን የመሙላት ስራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም የመንግስት ተቆጣጣሪ አካላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማድረግ በትብብር የሚሰራ ስራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም