የሕዳሴው ግድብ ፈተናን በመቋቋም ደማቅ ታሪክ መጻፍ ያስቻለ የጋራ ፕሮጀክታችን ነው-የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የሕዳሴው ግድብ ፈተናን በመቋቋም ደማቅ ታሪክ መጻፍ ያስቻለ የጋራ ፕሮጀክታችን ነው-የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች
አርባ ምንጭ፤ነሐሴ 21/2017 (ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውስጥና የውጭ ፈተናን በመቋቋም ደማቅ ታሪክ መጻፍ ያስቻለ እና ይቻላልን በተግባር ያሳየንበት የጋራ ፕሮጀክታችን ነው ሲሉ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች የሕዳሴው ግድብ ህዝቡን ከዳር ዳር ያስተሳሰረ ሌላኛው አድዋ መሆኑን ገልጸው፣ የሕዳሴውን ስኬት በሌሎች ልማቶችም መድገም ይገባል ብለዋል።
የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪና የጋሞ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ሃላፊ አቶ ታከለ ሀሚሶ እንደገለጹት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በገንዘባቸው፣ በዕውቀታቸውና በላባቸው የገነቡት የጋራ ሀብት ነው።
ለግድቡ ግንባታ ለአራት ጊዜ የወር ደመወዛቸውን ከመለገስ ባለፈ በተለያዩ የገቢ ዘርፎች በመሰማራት የድርሻቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
አያቶቻችን አንድነታቸውን በማጠናከር በአድዋ ጦርነት ታላቅ ድል በጋራ እንዳስመዘገቡት ሁሉ ግድቡም መላው ኢትዮጵያውያንን አስተሳስሮ በልማት አንድ ያደረገ የዘመኑ አድዋ ነው ብለዋል።
በተለያዩ ጊዜያት ግድቡ እውን እንዳይሆን ሲደረጉ የነበሩ የውጭና የውስጥ ጫናዎችን በመቋቋም ደማቅ ታሪክ መጻፍ ያስቻለና አይቻልምን በይቻላል የቀየረ የጋራ ሀብት መሆኑንም ተናግረዋል።
የሕዳሴው ግድብ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በሃይል አቅርቦት ላይ ያለውን ችግር በማቃለል ሀገርና ህዝብን በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ ያደርጋል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።
በልማት አርበኝነት የጋራ ደማቅ ታሪክ ከተጻፈበት የሕዳሴው ግድብ ስኬት በመማር ለሀገር ኢኮኖሚና ማህበራዊ ዕድገት የማይተካ ሚና ያላቸውን ፕሮጀክቶች ለማሳካት አንድነትን ማጽናት ይገባል ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውስጥና የውጭ ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር የይቻላል መንፈስን በህዝብ ላይ ያሰረጸ የጋራ ፕሮጀክታችን ነው ያሉት ደግሞ በአርባ ምንጭ ከተማ የሲቀላ ሙሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አርጋቸው አሻ ናቸው።
ግድቡ የህዝብን አብሮነት ከማስተሳሰር ባለፈ ፍትሃዊና የጋራ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸው፣ ከግድቡ ግንባታ ጀምሮ የትምህርት ቤቱ መምህራንና ተማሪዎች በተለያየ ጊዜ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ዜጎች በአንድነት የደከሙበት ግድብ ዛሬ ለፍሬ በመብቃቱ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ ግድቡ እንደሀገር ለተጀመረው የብልጽግና ጉዞ መሳካት ሚናው የጎላ መሆኑንና በቀጣይም የልማት ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።
ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ሰብለወንጌል ከበደ በበኩላቸው ግድቡ የአይቻልም አስተሳሰብን በይቻላል የቀየረ የዛሬው ትውልድ የልማት ድል መሆኑን ነው የተናገሩት።
መንግስት ግድቡ በቅርቡ እንደሚመረቅ ይፋ ማድረጉን ሲሰሙ መደሰታቸውን ያስታወሱት ነዋሪዋ፣ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያሳተፈው የሕዳሴው ግድብ፣ የኢትዮጵያዊያን የኩራት ምንጭ መሆኑንም ተናግረዋል ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በቅርቡ እንደሚመረቅ መንግስት ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።