ቀጥታ፡

አርሶ አደሮች  ምርታማነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ የኩታ ገጠም አሰራርን አጠናክረው  ቀጥለዋል

ነቀምቴ፤ ነሐሴ 21/2017(ኢዜአ)፡-የምሥራቅ ወለጋ ዞን አርሶ አደሮች ምርትና  ምርታማነታቸውን  ይበልጥ ለማሳደግ የኩታ ገጠም አሰራርን አጠናክረው መቀጠላቸው ተገለጸ።

በዞኑ በተያዘው የምርት ዘመን እየለማ ከሚገኘው 700ሺህ  ሄክታር መሬት ውስጥ 134ሺህ ሄክታር መሬት የበቆሎ ሰብል በኩታ ገጠም እየለማ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

አርሶ አደር ቶሌራ ያሲን  በዞኑ የጉቶ ጊዳ ወርዳ ነዋሪ ሲሆኑ፤ በዘንድሮ ክረምት  ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር ተቀናጅተው  በኩታ ገጠም በቆሎ እያለሙ  እንደሚገኙ ለኢዜአ ተናግረዋል። 

የኩታ ገጠም አሰራር ጊዜና ጉልበትን በመቆጠብ  ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቁመው፤ ይህም ከዚህ በፊት በተናጠል  እያለሙ ከቆዩት የተሻለ መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላኛው አርሶ አደር ኢታና ጊሎ ፤ ቀደም ሲል በኩታ ገጠም በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የአካባቢው አርሶ አደሮችም ጥቅሙን በመረዳት ከሳቸው ልምድ ወስደው  በኩታ ገጠም ማምረት መጀመራቸውን አንስተዋል።

የኩታ ገጠም አስተራረስ  ዘዴ  በተቀናጀ እና በህብረት በማልማት ምርትን በማሳደግ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን የተናገሩት አርሶ አደሮቹ፤  አሰራሩን አጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።


 

በምሥራቅ ወለጋ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት የሰብል እንክብካቤ እና ልማት ክፍል ሀላፊ አቶ ፍንታ አሰበ፤  በምርት ዘመኑ 700ሺህ ሄክታር መሬት በተለያየ የሰብል ዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።

ከዚህም ውስጥ  134ሺህ ሄክታር መሬት በቆሎ ሰብል በኩታ ገጠም የለማ መሆኑን ጠቅሰው፤ አጠቃላይ በምርት ዘመኑ ከሚለማው  መሬት  ከ23 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።

ለአርሶ አደሮቹ በተደረገላቸው የግንዛቤ ትምህርትና ድጋፍ በኩታ ገጠም የማልማት ተነሳሽነታቸው እየጨመረ መምጣቱን አንስተው፤ በጋራ በመስራት ውጤታማ እየሆኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

አምና ከለማው የበቆሎ ምርት ጥሩ ምርት መገኘቱን አስታውሰው፤  ዘንድሮም ከዚሁ ሰብል የተሻለ ምርት እንደሚጠበቅ  ገልጸዋል።

የዞኑ አርሶ አደሮችን ምርታማነት ይበልጥ ለማሳደግ ከድጋፍና ክትትል በተጨማሪ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ከወዲሁ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም