በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በትምህርት ዘርፍ የሚስተዋሉ ስብራቶችን ለመጠገን ለትምህርት ጥራት ማሻሻያ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በትምህርት ዘርፍ የሚስተዋሉ ስብራቶችን ለመጠገን ለትምህርት ጥራት ማሻሻያ ትኩረት ተሰጥቷል

አሶሳ፤ ነሐሴ 21/2017 (ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በትምህርት ዘርፍ የሚስተዋሉ ስብራቶችን ለመፍታት ለትምህርት ጥራት ማሻሻያ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ።
"የትምህርት ፍትሃዊነት እና ጥራት ለትውልድ ግንባታ" በሚል መሪ ሐሳብ ክልል አቀፍ የትምህርት ንቅናቄ መድረክ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ተካሄዷል።
በመድረኩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን እንደተናገሩት፤ ትምህርት ለሁሉን አቀፍ ዕድገት መሠረት የሚጥል እና ከጊዜው ጋር የሚራመድ የሰው ሃይል ለማፍራት ቁልፍ መሳሪያ ነው።
የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የተጀመሩ ሀገራዊ የሪፎርም ስራዎች በክልሉ ውጤታማ እየሆኑ በመምጣታቸው በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች በሂደት መሻሻል እያሳዩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተለይም ዘርፉን ከቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር እየተከናወኑ የሚገኙ የትምህርት እና የፈተና አሰጣጥ ሂደቶች ለትምህርት ጥራቱ መሻሻል ዓይነተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው ብለዋል።
በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመው፤ በተለይም የትምህርት ቤት ምገባ ለትምህርት ተደራሽነት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ማህበረሰቡን በማስተባበር ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
የትምህርት ቤቶች ደረጃን በማሻሻል ለመማር ማስተማር ምቹ እንዲሆኑ ማድረግ እና መምህራን ትውልድ ቀረፃ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያሳድጉ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል ።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ተመስገን ዲሳሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በክልሉ ከትምህርት ገበታ ውጪ የነበሩ ህፃናትን ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ እና ተዘግተው የነበሩ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ በማድረግ በኩል መሠራቱን ገልጸዋል።
በክልሉ 74 ትምህርት ቤቶች የምገባ ፕሮግራም እያካሄዱ መሆኑን ጠቅሰው ይህም የተማሪዎችን የትምህርት ተሳትፎ እንዲጨምር አድርጓል ነው ያሉት።
በ2018 የትምህርት ዘመን ለትምህርት የደረሱ ህፃናት ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ለማድረግ ቢሮው ከወዲሁ ዝግጅት እያደረገ ነው ያሉት ኃላፊው ዘርፉ የሁሉንም ተሳትፎ ይጠይቃል ብለዋል።