ሰላምን በማስጠበቅ ሁለንተናዊ እድገትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሰላምን በማስጠበቅ ሁለንተናዊ እድገትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው

ሆሳዕና ፤ ነሐሴ 21/2017(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላምን በመፍጠር የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ገለፀ፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና የፀጥታ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በተገኙበት "ሰላምን ማፅናት ለክልሉ ሁለንተናዊ ብልፅግና " በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የክልሉ ፀጥታ ምክር ቤት ጉባኤ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
የቢሮው ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ በዚህ ወቅት እንዳሉት፡ ለሁሉም ነገር መሰረት የሆነውን ሰላም በማስጠበቅ ሁለንተናዊ እድገትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው፡፡
የክልሉ መንግሥት ዘላቂና አስተማማኝ ሰላምን በመፍጠር ዜጎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው የሚኖሩበት ምቹ አካባቢ ለመፍጠር አሳታፊ በሆነ መልኩ ያከናወናቸው ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የክልሉን ህዝብ አብሮ የመልማትና የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የማህበረሰቡን አብሮነት፣ ነፃነትና እኩልነት የሚያስጠብቁ አሰራሮችን ዘርግቶ በመተግበር ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ የማህበረሰቡን ዘላቂ ሰላም ለማስጠበቅ፣ የህግ የበላይነትን በማስከበር ህገ ወጥነትንና ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል በሚረዱ ጉዳዮች ላይ የሚሰራ የፀጥታ ምክር ቤት በማቋቋም ወደ ትግበራ ምዕራፍ ተገብቷል ብለዋል፡፡
በዚህም በፀጥታ ችግር የተነሳ የመንግሥት አገልግሎት ሳያገኙ የቆዩ በርካታ ቀበሌያት አገልግሎት እንዲያገኙ ስለመደረጉም ለአብነት አንስተዋል፡፡
ቢሮው በክልሉ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም በመፍጠር የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚያስቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዞን አስተዳዳሪዎች የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት አባላት፣ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች እየተሳተፉ ነው፡፡