ቀጥታ፡

ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍን ለመከላከል አባል ሀገራት ብሔራዊ አጀንዳቸው አድርገው ሊሰሩ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 21/2017(ኢዜአ)፦ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍን ለመከላከል አባል ሀገራት ብሔራዊ አጀንዳቸው አድርገው በትብብር መስራት እንዳለባቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር እና የጸረ ህገ ወጥ የገንዘብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ ኮሚቴ ሊቀ መንበር ዓለምፀሀይ ጳውሎስ ገለጹ።

የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን 50ኛው የከፍተኛ ባለሙያዎች፣25ኛው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ እና ስምንተኛው የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የውይይት ፎረም በአዲስ አበባ አፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን እየተካሄደ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር እና የጸረ ህገ ወጥ የገንዘብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ ኮሚቴ ሊቀ መንበር ዓለምፀሀይ ጳውሎስ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍን ለመከላከል በቡድኑ ሀገራት መካከል ጠንካራ ትብብር ሊኖር ይገባል።


 

ስብሰባው በጋራ ከመምከር ባለፈ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመቆጣጠር የፋይናንስ ስርዓቱን ለማዘመንና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የጋራ ቁርጠኝነት መኖሩ የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።

የቡድኑ አባል ሀገራት በችግሮች ላይ በመምከር የጋራ መፍትሄ ማበጀት እንዳለባቸው በመጥቀስ፣በሀገራት መካከል ትብብር፣ተጠያቂነትና የቴክኒክ ልህቀት ሊኖር ይገባል ብለዋል።

እነዚህን ቀጣናዊ ችግሮች ለመከላከል የጋራ ተቋማትንና ቀጣናዊ ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍን መከላከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትኩረት የተሰጠው መሆኑን በመግለፅ፣ ተግባሩ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ አጀንዳ ነው ብለዋል።

ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍን መከላከል የሪፎርሙ አንዱ አጀንዳ መሆኑን ገልጸዋል።

በሀገራዊ ሪፎርሙ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ ብሔራዊ አጀንዳ በማድረግ እንደ ፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ያሉ ተቋማት እንዲጠናከሩ መደረጉን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በሀገራዊ ሪፎርሙ ለተቋማት ግንባት፣ለህግ ማስከበርና ለተጠያቂነት ስርዓት ትኩረት መስጠቷንም አስታውቀዋል።


 

በመርሀ ግብሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንክ ቁጥጥር ዳይሬክተር እና የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን የከፍተኛ ባለሙያዎች ግብረ ሀይል ሊቀ መንበር ፍሬዘር አያሌው፣የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን ፋይክል ዚታ፣ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሙሉቀን አማረን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ የዘርፉ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም