የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራዎች የበለጸገች አፍሪካን ለማሳካት ወሳኝ ሚና አላቸው-ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራዎች የበለጸገች አፍሪካን ለማሳካት ወሳኝ ሚና አላቸው-ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 21/2017(ኢዜአ)፦የሚዲና ኮሙኒኬሽን ሥራዎች የጋራ ትርክት በመገንባት፣የጋራ ማንነትን እና እጣ ፈንታን በማሳየት የበለጸገች አፍሪካን ለማሳካት ወሳኝ ሚና አላቸው ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ።
15ኛው የምስራቅ አፍሪካ የኮሙዩኒኬሽን ማህበር ጉባኤ"ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ለአፍሪካ ውህደት" በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ነው።
በጉባኤው ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ አፍሪካ በአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063፣ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና እና በተለያዩ አህጉራዊ ውጥኖች ወደ ጥልቅ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ባህላዊ ውህደት እየገሰገሰች ነው።
ቀጣናዊ እና አህጉራዊ ውህደትን እውን ለማድረግ የመሰረተ ልማት ትስስርን፣ ቀጣናዊ ትብብርን ማጠናከር እና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ጥልቅ የባህል ልውውጥ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራዎች የጋራ ትርክት በመገንባት፣የጋራ ማንነትን እና እጣ ፈንታን በማሳየት የበለጸገች አፍሪካን ለማሳካት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ገልፀዋል።
ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን የመረጃ ማሰራጫዎች ብቻ ሳይሆን የመግባቢያ ድልድዮች እና ሁሉን አቀፍ እና ሰላማዊ ማህበረሰቦችን ለመቅረጽ ምሰሶዎች እንደሆኑ ተናግረዋል።
ማህበሩ የሚዲያ እና የኮሙዩኒኬሽን ኢንዱስትሪ ችግሮችን ለመፍታት የመፍትሄ ሃሳቦችን በማቅረብ የበለጠ ጠንካራ ሚና መጫወት አለበት ብለዋል።
የዘርፉ ምሁራን የአፍሪካን ውህደት ለማጠናከር እና የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የመደመር መንገዶችን በማሳየት ጥረታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።