ትውልዱ የዘመናት የልማት ቁጭቱን በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ማሳካት ችሏል - ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ትውልዱ የዘመናት የልማት ቁጭቱን በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ማሳካት ችሏል - ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 21/2017(ኢዜአ)፦ትውልዱ በራሱ አቅምና በብርቱ ክንዱ የዘመናት የልማት ቁጭቱን በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማሳካት መቻሉን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
ኢትዮጵያ በዜጎቿ ትብብር እውን ያደረገችውን ግዙፉን የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በቅርቡ ዓለምን በሚያስደምም ድምቀት በልዩ ሁኔታ ለመመረቅ ዝግጅት እያደረገች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የግንባታ ስኬት አስመልክቶ "የኢትዮጵያ ማንሠራራት ጅማሮ፤ የደም ጠብታ፣ የላብ ጠብታ፣ የዕንባ ጠብታ፣ የውኃ ጠብታ ድምር ውጤት መሆኑን፣ ይህ ግድብ ህያው ምልክት ሆኖ ለትውልድ ሲመሰክር ይኖራል" በማለት መግለጻቸው ይታወቃል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት የሕዳሴ ስኬት በደምና በላብ የታሰረ የኢትዮጵያ የማንሰራራት መሰረት መሆኑን ያስገነዘበ ነው ብለዋል።
በቀጣይም ለኢትዮጵያ ብልጽግና ከሕዳሴ ግድብ በተጨማሪ ግዙፍ ዘርፈ ብዙ ስኬቶችን ማሳካት እንደሚቻል ያስረዳ መልዕክት መሆኑም አክለዋል።
ሕዳሴ ግድብ የቁጭት ፕሮጀክት ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ ኢትዮጵያ በውሃ ሃብቶቿ ለመጠቀም በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ሙከራዎችን ስታደርግ እንደነበር አውስተዋል።
የአሁኑ ትውልድ በራሱ አቅም ሕዳሴ ግድብን በብርቱ ክንድ እውን በማድረግ የኢትዮጵያን የዘመናት ቁጭት ያሳካና አኩሪ የልማት ገድል የፈጸመ ጀግና ትውልድ መሆኑን ተናግረዋል።
ግዙፉ የአፍሪካ ፕሮጀክት ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ስኬት ለቀጣዩ ትውልድ ጭምር ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ደማቅ የልማት አሻራ መሆኑን አብራርተዋል።
በፕሮጀክቱ ግንባታ ሂደት ከሀገር ውስጥ እስከ መላ ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ያለአንዳች ልዩነት በንቃት በመሳተፍ ደማቅ ታሪክ መፃፋቸውን አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ ፍትሐዊ የውሃ ሃብት አጠቃቀም ሥርዓት እንዲሰፍን አበክራ ስትሰራ መቆየቷን ገልጸዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ስኬትም ለዘመናት የቆየውን ኢ-ፍትሐዊ የውሃ ሃብት አጠቃቀም ስብራትን የሻረ አህጉራዊ ፕሮጀክት መሆኑን አንስተዋል።
የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት አስተማማኝ የውሃ ፍሰት እንዲያገኙ በማድረግ ሲያጋጥማቸው የነበረን የጎርፍ አደጋ ማስቀረት እንዳስቻለ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ግዙፉን የልማት ፕሮጀክት ያሳካችበት መንገድም ከተፋሰሱና ቀጣናው ሀገራት ተጠቃሚነት ባሻገር የአፍሪካ ሀገራት ልምድ ለመውሰድ ጥያቄ እያቀረቡ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የሕዳሴ ግድብ የተሸከመው ውሃም ከኃይል አቅርቦት ደጀንነት ባሻገር የዓሳ ሃብት በረከት፤ የኢኮ-ቱሪዝም መዳረሻ እየሆነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ከሌላቸው ቀንሰው የገንዘብ ድጋፍ ካደረጉ እስከ ህይወት መስዋዕትነት የከፈሉ ዜጎች ከትውልድ ትውልድ ሲዘከሩ እንደሚኖሩ ገልጸዋል።
የሕዳሴ ግድብ የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ሀገራዊና ቀጣናዊ የኃይል አቅርቦት ፍላጎትን ተደራሽነትን ለማስፋት ከፍተኛ አቅም መሆኑን አስረድተዋል።