ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የአምስት አመት የወጣቶች የሰላም የድርጊት መርሐ ግብር እየተዘጋጀ  ነው

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 21/2017(ኢዜአ)፦ወጣቶችን በሁለንተናዊ ዘርፍ  ተጠቃሚ የሚያደርግ የአምስት አመት የወጣቶች የሰላም የድርጊት መርሃ ግብር እየተዘጋጀ  መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ በሰላም ስራዎች ላይ የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም ወጣቶችን በፖለቲካ ኢኮኖሚና ማህበራዊ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚያደርግ የአምስት አመት የወጣቶች የሰላም የድርጊት መርሃ ግብር እየተዘጋጀ  መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሰላም የድርጊት መርሃ ግብሩ በውጭ የሚኖሩ ወጣቶችን ጭምር በማሳተፍ ለሰላም ግንባታ የሚያበረከቱትን ሚና ለማሳደግ ያስችላል ብለዋል፡፡

በተለይም ከወጣቶች ስብዕና ግንባታ ጋር በተያያዘ በዕቅድ የተቀመጡ ሰፋፊ ስራዎች መኖራቸውን አስታውቀዋል፡፡

በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የስራ ፈጠራ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ያስታወቁት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በተጠናቀቀው በጀት አመት ከተፈጠረው የስራ እድል 75 በመቶ የሚሆነው ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡

ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ በበጎ ፈቃድ ስራዎች ሰፊ ልዩነት የፈጠሩ በጎ ተግባራት በስፋት መከናወናቸውን አስረድተዋል፡፡

በዚህም በ2017 በጀት አመት 25 ነጥብ 9 ሚሊዮን ወጣቶች በበጎ ፈቃድ ባከናወኗቸው ስራዎች 25 ቢሊየን ብር የሚገመት አገልግሎት መስጠታቸውን ጠቅሰዋል።

ወጣቶቹ በወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃድ ስራ ህብረ-ብሄራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ስራዎች መስራታቸውንም አክለዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶች በአገሪቱ የሰላም፣የማህበራዊ ልማትና የፖለቲካ ጉዳዮች የሚያደርጉትን ተሳትፎ  አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

በግል ስራ የተሰማራው ወጣት ብሩክ መሰለ ወጣቶች በአገሪቱ እያደረጉት ያለውን ንቁ ተሳትፎና ገንቢ አስተዋጽኦ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብሏል።


 

የሚያጋጥሙ ችግሮችን ቁጭ ብሎ በመነጋገር የመፍታት ልምድን ማሳደግ እንደሚገባ ነው የገለጸው።

በኢትዮጵያ ስካውት ማህበር የወጣቶች ፎረም ሰብሳቢ ወጣት ያሬድ ሀይሉ ወጣቶች  በሰላም፣ በትምህርትና በሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው መቀጠላቸውን ተናግሯል።


 

ወጣቶች በተለያዩ አገራዊ የልማት ስራዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ ከማድረግ ባለፈ የተገነቡ መሰረተ ልማቶችን በአግባቡ በመጠቀምና በመንከባከብ ሚናችንን ልንወጣ ይገባል ብሏል።

ተማሪ ቃልኪዳን አራጌ በበኩሏ ወጣቶች ለአገሪቷ የጀርባ አጥንት እንደመሆናቸው መጠን እምቅ ሀይላቸውን ለአገር ጥቅም ማዋል እንደሚገባ ጠቁማ፤ መንግስት የስራ ፈጠራዎችን በፋይናንስ ለመደገፍ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ማጠናከር አለበት ብላለች።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም