ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ የሚደረገው የቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ የሚደረገው የቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል
ሐረር/አሶሳ፤ ነሐሴ 21/2017(ኢዜአ)፦ የደሞዝ ማሻሻያ እንደሚደረግ መገለጹን ተከትሎ በሐረሪ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ የሚደረገው የቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ።
የሐረሪ ክልል ኢንተርፕራይዞች ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡስማኢል ዩስፍ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ቀደም ሲል በምርቶችና በሸቀጦች ላይ ተገቢ ያልሆኑ የዋጋ ጭማሪዎች የሚያደርጉ ነጋዴዎችን የሚቆጣጠር ግብረኃይል ተቋቁሞ እየሰራ ይገኛል።
የንግዱ ማህበረሰብም ምርትን ሳይደብቅና ያለ አግባብ የዋጋ ጭማሪ ሳያደርግ በተመጣጣኝ ዋጋ ሸቀጦችን በማቅረብ ገበያ የማረጋጋት ስራ እንዲያከናውን ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።
በዚህም የንግዱ ማህበረሰብ ላበረከተው አስተዋጽኦና የተቀናጀ ስራ ምስጋና ያቀረቡት ሃላፊው በቅርቡም ተጨማሪ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እንደሚዘጋጁ አመልክተዋል።
የደሞዝ ማሻሻያ እንደሚደረግ መገለጹን ተከትሎ የግል ጥቅምን በማስቀደም ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ግብረ ሃይሉ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል እንደሚያደርግ ጠቁመው ነጋዴውም ከዚህ አላስፈላጊ ተግባር እንዲቆጠብ አሳስበዋል።
ህብረተሰቡም በምርቶችና ሸቀጦች ላይ ያልተገባ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎች ሲያጋጥሙት ለቢሮው ጥቆማ በመስጠት ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በክልሉ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ የሚደረገው የቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጸው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ነው።
የቢሮው ኃላፊ አስር ኢብራሂም እንዳስታወቁት፤ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ለመንግስት ሰራተኞች ይደረጋል የተባለው የደመወዝ ጭማሪ በንግዱ ስርዓት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያሳድር ቢሮው የጀመረውን የክትትልና ቁጥጥር ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል።
የንግዱ ማህበረሰብ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ እና ምርትን የመደበቅ ተግባር እንዳይፈጽም የተቋቋመው ግብረሃይል በርካታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልፀው፤ መንግስት ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት መስጠቱን ጠቁመዋል።
የተቋቋመው ግብረ ኃይል ከፍትህ አካላት ጋር በመሆን የንግድ ስርዓቱ በህጋዊ መንገድ እንዲከናወን ያደርጋል ያሉት አቶ አስር፤ ህብረተሰቡ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ አካላትን ጥቆማ በመስጠት ተባባሪ እንዲሆን ጠይቀዋል።
መንግስት የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል እና የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በብዝሃ ዘርፍ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን የወሰነው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተጨባጭ ውጤት ማስገኘቱንም ገልጸዋል።
በዚህም የንግድ ስርዓቱ ዘመናዊ እና ህጋዊ መንገድን የተከተለ እንዲሆን አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።
የክልሉ የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ በመምጣቱም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አርሶአደሩ የግብርና ምርቶችን ወደ ገበያ በማቅረብ የገበያ ዋጋ የማረጋጋት ስራ ማከናወኑን ተናግረዋል።