ሞሮኮ ለፍጻሜ አለፈች - ኢዜአ አማርኛ
ሞሮኮ ለፍጻሜ አለፈች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2017(ኢዜአ)፦ በስምንተኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮና (ቻን) የግማሽ ፍጻሜ መርሃ ግብር ሞሮኮ ሴኔጋልን በመለያ ምት በማሸነፍ ለፍጻሜ ደርሳለች።
ማምሻውን በማንዴላ ብሄራዊ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ጆሴፍ ላዩስ ሳምብ በ16ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠረው ግብ ሴኔጋል መሪ ሆናለች።
ብዙም ሳይቆይ ሳቢር ቡጅሪን በ23ኛው ደቂቃ ከመረብ ላይ ያሳረፈው ጎል ሞሮኮን አቻ አድርጓል።
መደበኛው 90 ደቂቃ ግብ በአቻ ውጤት በመጠናቀቁ 30 ደቂቃ ተጨምሯል። በጭማሪው ሰዓት ግብ ባለመቆጠሩ ጨዋታው ወደ መለያ አምርቷል።
በዚህም የሁለት ጊዜ የቻን አሸናፊዋ ሞሮኮ 5 ለ 3 በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፋለች። ከማዳጋስካር ጋር ዋንጫውን ለማንሳት ትፋለማለች።
የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ሴኔጋል ክብሯን ማስጠበቅ አልቻለችም።
ዛሬ ቀን ላይ በተደረገው የመጀመሪያ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ማዳጋስካር ሱዳንን 1 ለ 0 ማሸነፏ ይታወቃል።
የፍጻሜው ጨዋታ ቅዳሜ ነሐሴ 24 ቀን 2017 ዓ.ም ይካሄዳል።
የግማሽ ፍጻሜ ተሸናፊዎቹ ሴኔጋል እና ሱዳን አርብ ነሐሴ 23 ቀን 2017 ዓ.ም ሶስተኛ ደረጃን ለማግኘት ይጫወታሉ።
በታንዛንያ፣ ኬንያ እና ዩጋንዳ ጣምራ አዘጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው ቻን በሀገር ውስጥ ሊግ የሚገኙ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት ውድድር ነው።