ማዳጋስካር ለፍጻሜ አለፈች - ኢዜአ አማርኛ
ማዳጋስካር ለፍጻሜ አለፈች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2017(ኢዜአ)፦ በስምንተኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮና (ቻን) የግማሽ ፍጻሜ መርሃ ግብር ማዳጋካስካር ሱዳንን 1 ለ 0 በማሸነፍ ለፍጻሜ ደርሳለች።
ማምሻውን በቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ በመደበኛው 90 ደቂቃ ግብ ባለመቆጠሩ 30 ደቂቃ ተጨምሯል።
በጭማሪው ሰዓት የ24 ዓመቱ አጥቂ ቶኪ ኒያና ራኮቶንድራይቤ በ116ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ጎል ማዳጋስካርን ባለድል አድርጋለች።
የማዳጋስካሩ ፌኖሃሲና ጊሌስ ራዛፊማሮ በ79ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።
በጨዋታው ማገባደጃና ጭማሪ ሰዓት ላይ የአንድ ተጫዋች ብልጫ ወስዳ የተጫወተችው ሱዳን እድሏን መጠቀም አልቻለችም። በአንጻሩ ማዳጋስካር ጠንካራ የአልሸነፍ ባይነት መንፈስ አሳይታለች።
ውጤቱን ተከትሎ ማዳጋስካር ለፍጻሜው ያለፈች የመጀመሪያ ሀገር ሆናለች። በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የፍጻሜ ተፋላሚ ሆናለች።
ሱዳን በቻን ተሳትፎዋ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፍጻሜ የማለፍ ህልሟ አልተሳካም።
ማዳጋስካር በፍጻሜው ከሴኔጋልና ሞሮኮ አሸናፊ ጋር ትጫወታለች። ሴኔጋል እና ሞሮኮ በአሁኑ ሰዓት ጨዋታቸውን እያደረጉ ይገኛል።