ቀጥታ፡

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተፋሰስ ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2017(ኢዜአ)፦በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተፋሰስ ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የግድቡ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሔ(ዶ/ር) ገለጹ።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ከሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር "አንድ እቅድ አንድ ሪፖርት ለተቀናጀ የዓባይ ተፋሰስ ልማት" በሚል መሪ ሀሳብ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የምክክር መድረክ አካሂዷል። 


 

የጽህፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በራሳችን አቅም ሀገራዊ ግቦቻችንን ማሳካት እንደምንችል ለዓለም ያሳየንበት  ነው ብለዋል።

ሕብረት፣ ቁርጠኝነት፣ አርበኝነት እና የይቻላል መንፈስ ግድቡን አሳክተውታል ያሉት ዶክተር አረጋዊ፥ በርካታ እንቅፋቶችን ተሻግሮ በኢትዮጵያውያን የጋራ ርብርብ የድል ችቦው ሊለኮስ ተቃርቧል ብለዋል።

ግድቡን በጋራ እንደገነባነው ሁሉ ከደለል ለመከላከል በጋራ የተፋሰስ ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ላይ እየተሰራ ያለው ስራ የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል።

የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፈዬራ ዲንሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው ግድቡ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሉዑላዊነቷን ለማረጋገጥ የጀመረችውን ጉዞ የሚያሳካ ግዙፍ መሰረተ ልማት መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

ዩኒቨርሲቲው ግድቡን ከደለል ለመጠበቅ የሚያስችሉ ስራዎችን  እየሰራ መሆኑን የገለፁት ፕሬዝዳንቱ፤  የቆላ ቀርከሃ እና ሌሎች ሀገር በቀል ችግኞችን በተፋሰሱ አካባቢዎች ላይ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት እየተከለ መሆኑን ተናግረዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም የሚያስችሉ  ተግባራትን  አጠናክሮ እንደሚቀጥልም  ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የውሃና መሬት ሃብት ልማት ማዕከል ተመራማሪ አማረ ባንቲደር (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የግድቡን ዘላቂ አገልግሎት ለማስጠበቅ የተፋሰስ እና የውሃ ሀብት ጥበቃ በተቀናጀ መልኩ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።


 

ግድቡን ለመጠበቅ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በምርምርና ጥናት የተደገፈ ስራዎችን ሊያጠናክሩ ይገባል ብለዋል።

የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራው የአካባቢ ስነ-ምህዳር እንዲጠበቅ ያስችላል ሲሉም ጠቁመዋል።

የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ካሳ ሻውል (ዶ/ር) በበኩላቸው  በተፋሰሱ አካባቢ የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመሆን አካባቢን መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። 


 

ለዚህም ደግሞ ተቋማት በትብብርና ቅንጅት መስራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት መልካሙ ዴሬሳ (ዶ/ር) ዘላቂ የሆነ የውሃ ፍሰት እንዲኖር ለማድረግ አካባቢን መጠበቅ ግዴታ መሆኑን አንስተዋል።


 

ዩኒቨርሲቲው በአካባቢ ጥበቃ ላይ እየሰራ ያለውን ስራ በማጠናከር ግድቡን በመጠበቅ የበኩሉን አበርክቶ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም