የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን የማጣሪያ ተጋጣሚዎቹን አውቋል 

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በ2025/26 የካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ሀገራት የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) ዞን ማጣሪያ በምድብ ሁለት ተደልድሏል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የቻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ዕጣ ማውጣት ስነ ስርዓት ዛሬ በተቋሙ ዋና መቀመጫ ግብጽ ዋና ከተማ ካይሮ ላይ አከናውኗል።

ኢትዮጵያን በሴካፋ ዞን ወክሎ በማጣሪያ ውድድሩ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በምድብ ሁለት ከብሩንዲው ቶፕ ገርልስ አካዳሚ እና ከሩዋንዳው ራዮን ስፖርትስ ተደልድሏል።

የኬንያው ኬንያ ፖሊስ ቡሌትስ፣ የኤርትራው ደንደን እና የዩጋንዳው ካምፓላ ኩዊንስ በምድብ አንድ የተደለደሉ ክለቦች ናቸው።

በምድብ ሶስት የታንዛንያው ጄኬቲ ኩዊንስ፣ የደቡብ ሱዳኑ ዬ ጆይንት ስታርስ እና የዛንዚባሩ ጄኬዩ ፕሪንሰስ ክለቦች በምድብ ሶስት ተደልድለዋል። 

የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ከነሐሴ 29 2017 ዓ.ም እስከ መስከረም 6 ቀን 2018 ዓ.ም በኬንያ አዘጋጅነት ይካሄዳል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በማጣሪያ ውድድሩ የሚሳተፈው የዘንድሮው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ ነው።



ንግድ ባንክ በካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ሲሳተፍ የዘንድሮው ለአምስተኛ ተከታታይ ዓመት ነው። 

ክለቡ ከዚህ ቀደም ባደረጋቸው አራት ተሳትፎዎች በ2016 ዓ.ም የሴካፋ ዞን ማጣሪያን በማሸነፍ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ መሳተፉ የሚታወስ ነው። 

ካፍ በዘንድሮው የማጣሪያ ውድድር 38 ክለቦች በስድስት ዞኖች ተከፍለው ጨዋታቸውን እንደሚያደርጉ አስታውቋል።ክለቦቹ የካፍ የክለብ ላይሰንሲንግ መስፈርቶችን ማሟላታቸውንም ገልጿል።

በስድስቱ ዞኖች የሚያሸንፉ 6 ሀገራት፣ የወቅቱ የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎው ቲፒ ማዜምቤ አና የውድድሩን የመጨረሻ ዙር የምታዘጋጀው ግብጽ አንድ ቡድን ጨምሮ 8 ክለቦች እ.አ.አ በ2026 ዋንጫውን ለማንሳት ይፋለማሉ።

የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የተጀመረው እ.አ.አ በ2020 ነው።

የደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሳንዳውንስ ሁለት ጊዜ ዋንጫውን ያነሳ ሲሆን የሞሮኮው ኤኤስ ፋር ራባት እና የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎው ቲፒ ማዜምቤ ውድድሩን አንድ አንድ ጊዜ አሸንፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም