ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ትራንስፖርት ተሞክሮዋን በሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ ታቀርባለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ትራንስፖርት ተሞክሮዋን በሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ ታቀርባለች
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ትራንስፖርት ስርዓት ትግበራ የተመዘገቡ ውጤታማ የካርበን ልቀት ቅነሳ ተሞክሮዎቿን በሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ እንደምታቀርብ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ገለጸ።
የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ተጽዕኖ የማይበገር የትራንስፖርት ስትራቴጂ በማውጣት ባለፉት ሶስት ዓመታት ውጤታማ ተግባራት ማከናወኗን ገልጸዋል፡፡
በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ በማድረግና በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን የማስፋት ሥራ ለአየር ንብረት ለውጥ ተግባራዊ ምላሽ እየሰጠች ነው ብለዋል፡፡
እስካሁን ባለው ሂደት በሀገሪቱ ከ115 ሺህ በላይ የኤሌክትሪክ መኪኖች አገልግሎት እየሰጡ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ይህንን ተግባር ለማስፋት አስፈላጊ የመሰረተ ልማት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የተለያዩ አካላትን በማሳተፍ የተሽከርካሪዎች ኃይል መሙያ ጣቢያዎች በአዲስ አበባና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመገንባት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡።
በሌላ በኩል አሥራ ስድስት የኤሌክትሪክ መኪና መገጣጠሚያዎች ስራ መጀመራቸውን ገልጸው በቀጣይም በነዳጅ የሚሰሩ መኪና መገጣጠሚያዎች ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መገጣጠሚያ እንዲቀየሩ መመሪያ መሰጠቱን አንስተዋል፡፡
የአረንጓዴ ትራንስፖርት ስርዓት በህዝብ ትራንስፖርት ላይ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው፥ የኤሌክትሪክ አውቶብሶችንና ባቡሮችን የማስፋፋት ውጤታማ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ከትራንስፖርት የሚወጣውን የካርቦን ልቀት ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ መቻሏን ጠቁመዋል፡፡
ይህንን ውጤታማ ከብክለት የጸዳ የአረንጓዴ ትራንስፖርት ስርዓት ተሞክሮዋን ከጳጉሜን 3-5/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሚካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ ላይ እንደምታቀርብም ነው ያነሱት።
በትራንስፖርት ዘርፉ ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለመስጠት ፖሊሲና ስትራቴጂ ተቀርጾላቸው በውጤታማነት እየተተገበሩ የሚገኙ ተግባራትን ለጉባኤው ተሳታፊ ሀገራት እንደምታስተዋውቅ ጠቁመዋል።
ጉባኤው ኢትዮጵያ የምታከናውነውን ተግባር በተጨባጭ ከማሳየት በዘለለ በዘርፉ የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል።