ቀጥታ፡

የደመወዝ ጭማሪውን ተከትሎ  በክልሉ  ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር የተጠናከረ  ቁጥጥር እየተደረገ ነው

ባሕርዳር፤  ነሐሴ 20/2017 (ኢዜአ)፡- የመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ጭማሪን ተከትሎ በፍጆታ ምርቶች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር  የተጠናከረ  ክትትልና የቁጥጥር ስራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

ባለፈው በጀት ዓመት ገበያን ለማረጋጋት ከ4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ግምት ያላቸው የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች ለሕብረተሰቡ በተመጣጣን ዋጋ በትስስር ማቅረብ መቻሉም ተመላክቷል።

የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ  ምክትል ኃላፊ አቶ ፈንታው ፈጠነ፤ መንግስት ከመጪው መስከረም ወር  ጀምሮ የደመወዝ ጭማሪ እንደሚያደርግ ይፋ መሆኑን ተከትሎ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት የተቀናጀ ቁጥጥር እየተከናወነ ነው።

ለዚሕም በክልል ደረጃ ቀደም ብሎ የተቋቋመው የምርትና ግብይት፤ የገበያ አረጋጊ፤ የፀረ- ኮንትሮባንድና ሕገወጥ ንግድ ቁጥጥር ጥምር ግብረ ኃይል ጋር ቢሮው  እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ሕገወጥ ነጋዴዎች ላይ አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጅት መደረጉንም አስታውቀዋል።

ሕብረተሰቡም በመሰረታዊና በፍጆታ ምርቶች ላይ ባልተገባ መልኩ ዋጋ ለመጨመር የሚሞክሩ አካላት ሲያጋጥመው  ለሚመለከተው አካል ጥቆማ ሊያደርግ እንደሚገባም  አሳስበዋል።

ባለፈው የበጀት ዓመት ገበያን ለማረጋጋት ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ ተመድቦ  ከ4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለሕብረተሰቡ በተመጣጣን ዋጋ ማቅረብ መቻሉን አመልክተዋል።

እንዲሁም ከ25 ሚሊዮን ሊትር በላይ የምግብ ዘይትና ሌሎች የፍጆታ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ መደረጉን አውስተው፤ በአዲሱ በጀት ዓመትም ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የግብረ ኃይሉ አባልና የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው በበኩላቸው፤  ሕገወጥ ንግድን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ግብረ ኃይሉ የተጠናከረ ክትትልና ቁጥጥር  በቅንጅት እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በተለይም መንግስት ከቀጣዩ ወር ጀምሮ ያደረገውን የደመወዝ ጭማሪን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ምርትን በመደበቅና በማከማቸት እጥረት ለመፍጠርና ዋጋን ለማናር የሚሞክሩትን ስርዓት የማስያዙ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አብራርተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም