የኮንትሮባንድ ንግድ እንቅስቃሴን ለመግታት የቁጥጥር ተግባሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የኮንትሮባንድ ንግድ እንቅስቃሴን ለመግታት የቁጥጥር ተግባሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል
ሚዛን አማን፤ ነሐሴ 20/2017 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የኮንትሮባንድ ንግድ እንቅስቃሴን ለመከላከል የቁጥጥር እና እርምጃ ተግባር እንደሚጠናከር የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት የኮንትሮባንድና ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር በተወሰደ ርምጃ ከ48 ሚሊዮን ብር በላይ ወደ መንግስት ካዝና ለማስገባት መቻሉን ቢሮው አስታውቋል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ተመስገን ከበደ ለኢዜአ እንደገለጹት ኮንትሮባንድ የሕዝብና የመንግሥት ገቢን ወደ ራስ በማዞር የሀገር ኢኮኖሚን የሚጎዳ እኩይ ተግባር ነው።
የሕዝብ ጥያቄ በወቅቱ ተገቢ ምላሽ እንዳያገኝ ምክንያት መሆኑን ገልጸው፤ በክልሉ በማዕድን፣ በቡናና መሰል የኤክስፖርት ምርቶች ላይ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ጎልቶ እየታየ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ በክልሉ ለማዕድን ምርት ማውጣት ለማሽን ሥራዎች ከፍተኛ ነዳጅ ማስፈለጉን ተከትሎ የኮንትሮባንድ ንግድ ከሚፈጸምባቸው ምርቶች 60 በመቶ በነዳጅ ላይ መሆኑን አስረድተዋል።
ሰው ሰራሽ የነዳጅ እጥረቱ ለትራንስፖርት ታሪፍ መጨመር፣ የምርት አቅርቦት እንዲዘገይና የምርቶች ዋጋን እንዲጨምር በማድረግ የገበያ ሥርዓቱን እያናጋው መሆኑንም አቶ ተመስገን ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ ቡናን ጨምሮ በሌሎች የኤክስፖርት ምርቶች ላይ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በክልሉ በስፋት ይስተዋላል ያሉት ኃላፊው ይህም በመንግሥት ገቢና ወጪ ምርት ምጣኔ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው ብለዋል።
በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት እነዚህን ህገወጥ ተግባራት ለመቆጣጠር በተደረገ ጥረት ከ48 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ወደ መንግስት ካዝና ገቢ ለማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል።
በቀጣይ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴውን ለመቆጣጠር የህብረተሰቡን ተሳትፎ ከማጠናከር ባለፈ በተቋቋሙ ልዩ የፍተሻ ኬላዎች ላይ በግብረሀይል ጠንከር ያለ ቁጥጥር በማድረግ የማያዳግም እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
ለሕገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ተባባሪ በሆኑ የመንግሥት ሥራ አመራሮችና ባለሙያዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወሰድ የጠቀሱት ሃላፊው፣ ግለሰቦችን በግምገማ የማጥራት ሥራ መጀመሩንም ጠቁመዋል።
በኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡ የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪ መካከል አቶ ማርሸት ክፍሌ እንደገለጹት ኮንትሮባንድ የጥቂቶችን ኪስ በማደለብ የብዙዎችን ኑሮ እየጎዳ ነው።
የጥቂት ራስ ወዳድ ነጋዴዎችን እንቅስቃሴ ለመግታት በመንግስት የሚወሰድ እርምጃ ጠንከር ያለ መሆን እንዳለበትም ተናግረዋል።
በተለይ በነዳጅ ላይ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ እየጎላ መምጣት በተለያዩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ላይ መስተጓጎል በመፍጠር በዜጎች የእለት ተዕለት ኑሮ ላይ ከፍትኛ ጫና እያሳደረ መሆኑን አመልክተዋል።
በመሆኑም የተቀናጀና ቀጣይነት ያለው የቁጥጥር መረብ ዘርግቶ ማኅበረሰቡን ከበዝባዦች መታደግና እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ሚዛን መጠበቅ ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸው፣ ድርጊቱን ለመከላከልና ለማስቆም በሚደረግ ጥረት የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ እና ሕገወጥ ንግድን ለማስቀረት የሁላችንም ተሳትፎ መጠናከር አለበት ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ጽዮን ሰሎሞን የተባሉ ነዋሪ ናቸው።
እንደነዋሪ በዚህ ተግባር የሚሳተፉትን ህብረተሰቡ ጠቁሞ አሳልፎ ከሰጠና የሚመለከተው አካልም ተገቢና አስተማሪ እርምጃ ከወሰደ ማስተካከል ይቻላል የሚል እምነት እንዳላቸው አክለዋል።