የሕዳሴው ግድብ በቅርቡ እንደሚመረቅ መገለጹ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ብርታትና አቅም ነው--የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የሕዳሴው ግድብ በቅርቡ እንደሚመረቅ መገለጹ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ብርታትና አቅም ነው--የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች
ደሴ፤ነሐሴ 20/2017 (ኢዜአ)፡-ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ በቅርቡ እንደሚመረቅ መገለጹ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ብርታትና አቅም ነው ሲሉ የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ነዋሪዎቹ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ ለፍፃሜ የደረሰው የሕዳሴ ግድብ የአይቻልም አስተሳሰብን የቀየረ ከመሆኑም በላይ ተጨማሪ መሰል ፕሮጀክቶችን ለማሳካት ብርታት እንደሚሰጥም ተናግረዋል።
የሕብረ ብሔራዊ አንድነት ቁልፍ ማሳያ በመሆኑና ህዝብን ለአንድ ዓላማ ያሰለፈ ከመሆኑም በላይ ለሀገራዊ እድገት ጉልህ አስተዋጾ ስላለው እንደዓይን ብሌናቸው እንደሚጠብቁትም ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡ የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ሸህ አሊ እንድሪስ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የሕዳሴ ግድቡ የሁሉም ኢትየጵያዊ አሻራ ያረፈበት የጋራ ታሪክ መሆኑን ጠቅስዋል።
የአንድነታችን ገመድ፣ የአይበገሬነታችን ማሳያ እና የብልጽግናችን ተስፋ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በአብሮነት የተገነባና የጀግንነት መገለጫ ግድብ መሆኑን ጠቁመው ለሀገር ልማት ካለው ፋይዳ አንጻር እንደ ዓይን ብሌናቸው እንደሚያዩት ገልጸዋል።
የግድቡ መመረቅ ዜና ለዓመታት ለሕዳሴው ግድብ ድጋፍ ሲያደርጉ ለነበሩ ኢትጵያውያን ትልቅ ብርታትና አቅም መስጠቱን ገልጸው፣ በቀጣይ ለሀገር የልማት ፕሮጀክቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ መነሳሳት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።
ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ አረጋ ብርሃኑ በበኩላቸው እንዳሉት የሕዳሴው ግድብ ግንባታው ተጠናቆ የሚመረቅበትን ዕለት በጉጉት ሲጠብቁ ቆይተዋል።
የለውጡ አመራር በወሰደው እርምጃና ለመፍትሄው በመስራቱ ከገጠመው ውስብስብ ችግር በማውጣት ዛሬ ላይ ለምረቃ በመድረሱ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለሕዳሴ ግድብ እስከዛሬ ድረስ ከ10 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን የተናገሩት አቶ አረጋ በቀጣይም ህዝብና ሀገርን ተጠቃሚ ለሚያደርጉ የልማት ፕሮጀክቶችም ድጋፋቸውን አጠናከረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የሕዳሴው ግድቡ በኢትዮጵያውያን ላይ የይቻላል መንፈስ የፈጠረ፣ አንድነታችንን ያስተሳሰረና በራስ አቅም የተገነባ ፈር ቀዳጅ ፕሮጀክታችን ነው ያሉት ደግሞ አቶ ሰይድ አሊ የተባሉ ነዋሪ ናቸው።
ግድቡ ተጠናቆ በቅርቡ እንደሚመረቅ መገለጹ ለመላው ኢትዮጵያውያን ትልቅ ብስራት፣ ጉልበትና አቅም መሆኑን ገልጸው ለፍጻሜ በመቃረቡ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የግድቡ ግንባታ ህዝብን ለልማት በአብሮነት ያሰለፈ፣ አይቻልምን በይቻላል የቀየረና የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋገጥ በመሆኑ እንደራስ ሀብት እንደሚጠብቁት ገልጸዋል።
በሕዳሴው ግድብ በአራቱም ማዕዘን ያለን ኢትዮጵያዊያን በልማት በመተባበር ደማቅ ታሪክ ሰርተናል ያሉት ሰይድ፤ ግድቡን እንደ እርሾ በመውሰድ ሌሎች የልማት ሥራዎችን ለማሳካት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም ገልጸዋል።
ከዚህ ተሞክሮ በመውሰድ መንግስት ያቀዳቸውን የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ ነዳጅ እና ሌሎች ብሔራዊ ጥቅሞችን የሚያስጠብቁ ፕሮጀክቶች እውን እንዲሆኑ የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።