ኢትዮ-ቴሌኮም የዜጎችን ተጠቃሚነት መሰረት ያደረገ የሶስት ዓመት ሰው ተኮር አዲስ አድማስ ስትራቴጂ ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮ-ቴሌኮም የዜጎችን ተጠቃሚነት መሰረት ያደረገ የሶስት ዓመት ሰው ተኮር አዲስ አድማስ ስትራቴጂ ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮ-ቴሌኮም የዜጎችን ተጠቃሚነት መሰረት ያደረገ የሶስት ዓመት ሰው ተኮር አዲስ አድማስ ስትራቴጂ ይፋ አደረገ።
ተቋሙ ከ2018 እስከ 2020 ዓ.ም የሚተገበር የሶስት ዓመት የቀጣዩ አድማስ ስትራቴጂ እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅዱን ይፋ አድርጓል።
የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ አዲስ አድማስ የቀጣይ ሶስት ዓመት ስትራቴጂ አዲስ ጅማሮ አዲስ ተስፋ እና አዲስ ዕይታን የያዘ ነው።
ስትራቴጂው ብሔራዊ ስትራቴጂና ዕቅዶችን፣ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን እንዲሁም የፋይናንስ አካታችነትን ታሳቢ አድርጎ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
አዲስ አድማስ ስትራቴጂ ሰው ተኮር ራዕይ የያዘ በየዘርፉ የተያዙ ዕቅዶች እንዲሳኩ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።
ስትራቴጂው ትብብርና አንድነት፣ ልህቀት፣ ዕምነትና ጥምረት፣ ፈጠራና ማህበራዊ ሀላፊነትን ለማሳካት ያለመ አዲስ እይታ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን የዲጂታል ሽግግር ለማጠናከር ለዲጂታል ቴክኖሎጂ ቅድሚያ መስጠት እና የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት ማድረግ የቀጣይ ትኩረቶች መሆኑንም ጠቅሰዋል።
አዳዲስ እውቀትና ክህሎት የሚጠይቁ ቴክኖሎጂዎች የሚመጥን የሰው ሀይል ማፍራት፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ፈጣን አገልግሎት መስጠት፣ የሚተማመኑበት ተቋም መገንባት የስትራቴጂው ትኩረት መሆኑን ገልጸዋል።
የደንበኞችን እርካታ ማላቅ፣ ኦፕሬሽናል ልህቀትን ማሳደግ፣ የሰራተኞችን ብቃት መለካት እና የገበያ መሪነቱን ማረጋገጥ የስትራቴጂው ስኬታማነት መለኪያዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።