ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ሕብረት፣ አርበኝነት እና የይቻላል መንፈስ በተግባር የተረጋገጠበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ሕብረት፣ አርበኝነት እና የይቻላል መንፈስ በተግባር የተረጋገጠበት ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2017(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ሕብረት፣ ቁርጠኝነት፣ አርበኝነት እና የይቻላል መንፈስ በተግባር የተረጋገጠበት መሆኑን የግድቡ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ከሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር "አንድ እቅድ አንድ ሪፖርት ለተቀናጀ የዓባይ ተፋሰስ ልማት " በሚል መሪ ሀሳብ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።
የጽህፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በራሳችን አቅም ሀገራዊ ግቦቻችንን ማሳካት እንደምንችል ለዓለም ያሳየንበት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያውያን ሕብረት፣ ቁርጠኝነት፣ አርበኝነት እና የይቻላል መንፈስ በተግባር የተረጋገጠበት ነው ያሉት ዶክተር አረጋዊ፥ ግድቡ የድል ችቦው በጋራ የሚለኮስበት ምዕራፍ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።
የሕዳሴ ግድብ በርካታ እንቅፋቶችን ተሻግሮ በኢትዮጵያውያን የጋራ ርብርብ ለምረቃ መዘጋጀቱን ጠቅሰው፥ አዲስ ታሪክ የተሰራበትና በትውልድ የሚታወስ አኩሪ የተጋድሎ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል ።
ግድቡን በጋራ እንደገነባነው ሁሉ በደለል እንዳይሞላ በጋራ የተፋሰስ ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ላይ እየተሰራ ያለው ስራ የበለጠ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በማንሳት፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም በጥናትና ምርምር ሊደግፉ ይገባል ብለዋል።
የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፈዬራ ዲንሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው ግድቡ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ልዑላዊነቷን ለማረጋገጥ የጀመረችውን ጉዞ የሚያሳካ ግዙፍ መሰረተ ልማት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዩኒቨርሲቲው ግድቡን ከደለል ለመጠበቅ የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን የገለፁት ፕሬዝዳንቱ፤ የቆላ ቀርከሃ እና ሌሎች ሀገር በቀል ችግኞችን በተፋሰሱ አከባቢዎች ላይ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት እየተከለ መሆኑን ተናግረዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም የሚያስችሉ ተግባራትን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።