ቀጥታ፡

መንግሥት ፍትሃዊ የመንገድ መሰረተ ልማት እንዲስፋፋ የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነ ነው- ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ

ጅግጅጋ፣ ነሐሴ 20/2017 (ኢዜአ):- መንግሥት ፍትሃዊ የመንገድ መሰረተ ልማት እንዲኖርና እንዲስፋፋ  ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ። 

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር 2ኛው የመንገድ ዘርፍ ጉባዔ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ እየተካሄደ ነው። 


 

ከፌዴራል፣ ከክልሎች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የዘርፉን የ2017 ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማና  የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ  ጉባዔው  የሚያተኩርባቸው ናቸው።  

በጉባዔው መድረክ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፣ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፋ ሙሐመድን ጨምሮ ሌሎችም የፌዴራልና የክልል የመንገድ የዘርፉ  የሥራ ኃላፊዎችና የተጠሪ ተቋማት አመራሮች ተገኝተዋል። 

ሚነስትር ጫልቱ ሳኒ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፤  ጉባኤው ለሀገሪቱ ልማት መሳለጥ ከፍተኛ ሚና ባለው በመንገድ መሰረተ ልማት ላይ የሚመክር በመሆኑ ፋይዳው የጎላ ነው። 

የመንገድ ልማት ሀገሪቱ የምትከተለው የኢኮኖሚ  ልማት ዕቅዶች ግብ መድረስ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤  መንግሥት ፍትሃዊ የመንገድ መሰረተ ልማት እንዲኖርና እንዲስፋፋ  በትኩረት  እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከውበት ባለፈ ለመንገድ ሸፋን እድገትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ  እንዳላቸው ጠቅሰዋል።


 

"በጋራ ኢትዮጵያን እንገንባ" በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ ባለው ጉባዔ ላይ  ንግግር ያደረጉት የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ ሙሐመድ፤  ከለውጡ ወዲህ የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታን ከተስፋፋባቸው የሃገሪቱ አካባቢዎች መካከል  የሶማሌ ክልል  አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

ቀደም ብሎ ዞንና ዞን የሚያገናኙ መንገዶች ቅንጦት የሆኑበት ክልል አሁን ወረዳን ከወረዳና ከዞን የሚያገናኙ ሰፋፊ የመንገድ መሰረተ ልማቶች መገንባታቸውን ጠቅሰዋል። 

የከተማና የገጠር የኮሪደር ልማትም  በክልሉ የማስፋፋቱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም