በቻይና በተካሄደው የክህሎት ውድድር የተመዘገበው ውጤት በክህሎት ዘርፍ የማንሰራራት ብስራት ነው -ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል - ኢዜአ አማርኛ
በቻይና በተካሄደው የክህሎት ውድድር የተመዘገበው ውጤት በክህሎት ዘርፍ የማንሰራራት ብስራት ነው -ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2017(ኢዜአ)፦ በቻይና በተካሄደው የክህሎት ውድድር የተመዘገበው ውጤት ሀገራዊ የክህሎት ዘርፍ የማንሰራራት ድል ብስራት ነው ሲሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
የውድድሩ አሸናፊዎች ኢትዮጵያ በክህሎት ልማት እያከናወነች ያለውን አመርቂ ተግባር ለዓለም ያረጋገጡበት እንደሆነም ገልጸዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በቻይና በተካሄደው የክህሎት ውድድር አሸናፊ ለሆኑት ወጣቶች ትናንት በቢሯቸው አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ከብሪክስ አባል ሀገራት የተውጣጡ ከ300 በላይ ወጣቶች በተሳተፉበት የቻይና የክህሎት ውድድር ኢትዮጵያዊያን የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆነዋል።
ለ11ኛ ዙር በቻይና ጎዋንዡ በተካሄደው ውድድር ኢትዮጵያን የወከሉትና በተለያዩ ዘርፎች የፈጠራ ሀሳባቸውን ያቀረቡት ዘላለም እንዳለው አንደኛ፤ አቤኔዘር ተከስተ ሁለተኛ እንዲሁም ነቢሀ ነስሩ ሶስተኛ በመውጣት ነው ሜዳሊያቸውን ያገኙት።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚሁ ወቅት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከለውጡ ወዲህ መንግስት በሪፎርም ከለያቸው አጀንዳዎች አንዱ የክህሎት ልማት ነው።
ለክህሎት ልማት የተሰጠው ልዩ ትኩረት ፍሬ እያፈራ መምጣቱን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ በስልጠና ብቻ ሳይሆን በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ውጤት እየታየ መሆኑን ተናግረዋል።
በተሰሩት አበረታች ተግባራት በዓለም አደባባይ ሀገርን ማስጠራት የሚያስችል ውጤት እየተመዘገበ መምጣቱን በአብነት አነስተዋል።
የወጣቶች እምቅ አቅም ላይ መስራት ከተቻለ ለሀገርም ሆነ ለዓለም ችግር የበለጠ መፍትሄ የሚሰጡ የፈጠራ ሃሳቦችን ማፍለቅ እንደሚቻል ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በማንሰራራት ሂደት ውስጥ እንዳለች ያነሱት ሚኒስትሯ፤ በውድድሩ የተመዘገበው ውጤት የክህሎት ዘርፍ የማንሰራራት ድል ብስራት ነው ሲሉ ገልፀዋል።
በቻይና የተካሄደው የክህሎት ውድድር ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም ያሳየችበት መሆኑን ጠቅሰዋል።