በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር እስከ አሁን 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኝ ተተክሏል- የብሄራዊ አረንጓዴ አሻራ ቴክኒክ ኮሚቴ - ኢዜአ አማርኛ
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር እስከ አሁን 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኝ ተተክሏል- የብሄራዊ አረንጓዴ አሻራ ቴክኒክ ኮሚቴ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 19/2017(ኢዜአ)፦ በ2017 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር እስከ አሁን 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኝ መተከሉን የብሄራዊ አረንጓዴ አሻራ ቴክኒክ ኮሚቴ አስታወቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ ማስጀመራቸው ይታወቃል።
በመርሃ-ግብሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል እቅድ ተይዞ ወደ ስራ ተገብቷል።
የብሄራዊ አረንጓዴ አሻራ ቴክኒክ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው ግዛው እስከ ነሐሴ 16 ቀን 2017 ዓ.ም ባለው መረጃ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከ 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኝ በላይ በመትከል ከእቅድ በላይ ማሳካት መቻሉን ለኢዜአ ገልጸዋል።
የችግኝ ተከላው በሂደት ላይ በመሆኑ ቁጥሩ አሁን ካለበት ከፍ ሊል እንደሚችል ጠቅሰው ተከላው ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ላይ ያረፈ መሆኑን አመልክተዋል።
ከአረንጓዴ አሻራ ማርሃ-ግብር መጀመር በፊት ዓመቱን ሙሉ ሲከናወን የነበረው የቅድመ ዝግጅት ስራ አፈጻጸሙ ከእቅድ በላይ እንዲሳካ ማድረጉን ተናግረዋል።
በበጋው ወቅት የተከላ ቦታዎችን የመለየት፣ የተለዩ ቦታዎች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ የማከናወን፣ ከየአካባቢው አየር ንብረት ጋር የሚጣጣም ችግኞችን የማፍላትና የተለዩ ቦታዎች ላይ ካርታ የማዘጋጀት ስራ (ጂኦ-ሪፈረነስ) በስፋት መከናወኑን ነው ያስታወሱት።
የአቅም ግንባታ እና ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ መፍጠር መቻሉንም እንዲሁ።
ከዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ98 በመቶ በላይ ስራ መከናወኑን ገልጸው ዝናብ አስቀድሞ በገባባቸው ክልሎች የችግኝ ተከላው ስራ መጠናቀቁን ጠቁመዋል።
ዝናብ ዘግይቶ በጀመረባቸው በተለይም የምስራቅ የሀገሪቷ ክፍሎች ላይ የችግኝ ተከላው መቀጠሉን ነው አቶ ጌታቸው ያስረዱት።
በዘንድሮ መርሃ-ግብር ከተዘጋጁ ችግኞች መካከል 60 በመቶው ዘርፈ ብዙ ጠቃሜታ ያላቸውን ችግኞች የያዘ የጥምር ግብርና አዝዕርቶች መሆናቸውን ጠቅሰው ቀሪው 40 በመቶ ለደን አገልግሎትና ለኢንዱስትሪ ምርት የሚሆኑ ችግኞች መሆናቸውን ገልጸዋል።
የፍራፍሬና አትክልት ምርቶች ከባለፉት ዓመታት በተለየ ዘንድሮ የተሻለ ለውጥ እንደታየባቸውና የጫካ ችግኞችን የመትከል ስራ መከናወኑን አመልክተዋል።
እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ የዘንድሮውን ጨምሮ እስከ አሁን 47 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኝ በአረንጓዴ አሻራ ተተክሏል።
በመጀመሪያውና በሁለተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር 50 ቢሊዮን ችግኝ የመትከል እቅድ መያዙን ጠቅሰው እቅዱ አንድ ዓመት እየቀረው ያለው አጠቃላይ አፈጻጸም አመርቂ የሚባል መሆኑን አብራርተዋል።
ከዓመት ዓመት እያደገ የመጣው አረንጓዴ አሻራ ወደ ትልቅ ሀገራዊ ኢኒሼቲቭ ተሸጋገሯል ያሉት ምክትል ሰብሳቢው ሚሊዮኖች በመርሃ ግብሩ በነቂስ ወጥተው መሳተፋቸውና ከቴክኖሎጂ ጋር ይበልጥ መተሳሰሩ አቅሙ እንዲያድግ ማድረጉን አንስተዋል።
አረንጓዴ አሻራ ባህል እየሆነ መምጣቱን ገልጸው በቀጣይ የዜጎችን ባለቤትነት ማሳደግና የእንክብካቤ ስራውን የበለጠ የማጠናከር ስራ እንደሚከናወን ገልጸዋል።
የጥምር ግብርና በተለይም ለምግብ ዋስትና መረጋጋጥ ሚና የሚኖራቸውን ችግኞች ላይ የበለጠ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ አክለዋል።